Sunday, December 23, 2012

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና እነ አንዱዓለም አራጌ የይግባኝ ክርክራቸውን አጠናቀቁ!!!


ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና እነ አንዱዓለም አራጌ የይግባኝ ክርክራቸውን አጠናቀቁ!!!

        --------ኢሳትም የመገናኛ ብዙኃን እንጂ የአሸባሪ ድርጅት ሚዲያ አለመሆኑን ማረጋገጣቸውን <  አቶ ደርበው ገልጸዋል፡፡ 
--------ለአንድ ዓመት ከሦስት ወር መሬት ላይ እንዲተኛ መደረጉን
---------ትንሽ ብርሃን ባለበት በጨለማ ክፍል ውስጥ ከስድስት ሰዎች ጋር መታሰሩን
-------- የመተንፈስ ችግር እንዳለበት
---------ከተወሰኑ ቤተሰቦቹ በስተቀር ሌላ ሰው እንዳይጠይቀው መከልከሉን አስረድቷል
                                                                                                                            አንዱዓለም አራጌ
በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ ወንጀል ችሎት በሽብርተኝነት ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸው በ18፣ በ25 ዓመታትና በዕድሜ ልክ እስራት ተቀጥተው በእስር ላይ የሚገኙት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ ናትናኤል መኮንን፣ ክንፈሚካኤል አበበ (አበበ ቀስቶ) እና አንዱዓለም አራጌ ቅጣታቸውን በመቃወም ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ባቀረቡት የይግባኝ አቤቱታ ላይ ከዓቃቤ ሕግ ጋር ታህሳስ 10 ቀን 2005 ዓ.ም. ክርክር አድርገው አጠናቀቁ፡፡ አንዱዓለም አራጌ፣ ናትናኤል መኮንንና ክንፈሚካኤል አበበ (አበበ ቀስቶ) ክርክራቸውን ያደረጉት በጠበቃ ተወክለው ሲሆን፣ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ግን ክርክሩን ያደረገው ያለጠበቃ በራሱ ነው፡፡ 

ጋዜጠኛ እስክንድር ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያቀረበው ወይም ባደረገው ክርክር ላይ በዋናነት ያነሳው ነጥብ፣ የግንቦት 7 ድርጅት አባል ስለመሆኑ የተገኘበት መረጃም ይሁን የሰው ምስክር በዓቃቤ ሕግ እንዳልቀረበበትና “አባል ነው” መባሉም ፍፁም ሐሰት መሆኑን ነው፡፡ በሥር ፍርድ ቤትም በዋናነት ሲከራከርበት የነበረበትንና “የግንቦት 7 ዓባል ስለመሆኔ ዓቃቤ ሕግ ምንም ዓይነት ማስረጃ ባላቀረበብኝና ባልተመሰከረብኝ ሁኔታ እንዴት ልቀጣ እችላለሁ?” የሚለውን ሐሳብ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ባቀረበው የክርክር ሐሳብም በዋናነት ተናግሯል፡፡ 

ዓቃቤ ሕግ በሥር ፍርድ ቤት ላቀረበበት ክስ በዋና ማስረጃነት ያቀረበው  በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን የተናገራቸውንና የጻፋቸውን የተለያዩ መጣጥፎች፣ እሱን ጨምሮ ሰባት ሆነው ሊመሠርቱት ስለነበረ የሲቪክ ማኅበር መመሥረቻ ጽሑፍ እንጂ የሰው፣ የሰነድም ሆነ የኢ-ሜይል ማስረጃዎች እንዳልቀረቡበትና በፍፁም የግንቦት 7 ድርጅት አባል አለመሆኑን አስረድቷል፡፡  

ዓቃቤ ሕግ እንደ ዋና ማስረጃ ያቀረበበት በመስከረም ወር 2004 ዓ.ም. ሰላማዊ ሠልፍ ለማድረግ ሲንቀሳቀሱ ከነበሩት የመኢዴፓ ዋና ጸሐፊ ከአቶ ዘመኑ ሞላ ጋር ያደረገውን ንግግር መሆኑን ጋዜጠኛ እስክንድር አስረድቷል፡፡ አቶ ዘመኑ ወደሱ መጥቶ ሰለ ሰላማዊ ሠልፉ ምክር ሲጠይቀው፣ ሰላማዊ ሠልፍ ለማድረግ ወቅቱ እንዳልሆነ፣ ሠልፍ የሚያደርጉም ከሆነ በማንኛውም መንገድ የውጭ ኃይሎች እጅ ሊኖርበት እንደማይገባኧ የገንዘብ እጥረት ቢኖርባቸው እንኳን እሱም ቢሆን በገንዘብ ሊረዳቸው እንደሚችል ከመመካከር ውጭ፣ አንዲትም ቃል ስለአመፅና ረብሻ ተነጋግረው እንደማያውቁ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ አቶ ዘመኑም በሥር ፍርድ ቤት ለዓቃቤ ሕግ ምስክር ሆነው በቀረቡበት ወቅት ያረጋገጡት ይህንኑ መሆኑንና ፍርድ ቤቱ የሥር ፍርድ ቤት መዝገብን ሊመለከተው እንደሚገባ ጠቁሟል፡፡ 
ዓቃቤ ሕግ በሰሜን አፍሪካና በዓረብ አገሮች የተቀሰቀሰውን አመፅ ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ ነበር በማለት ስላቀረበበት ክስ ጋዜጠኛ እክስንድር ለፍርድ ቤቱ ሲያስረዳ፣ “ዓቃቤ ሕግ ይህንን ሐሳብ ወይም ክስ ያቀረበው እኔ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ያቀረብኳቸውን መጣጥፎች በግንቦት 7 ልሳን ላይ ስላገኛቸው እንጂ፣ ምንም ዓይነት እውነተኛ ማስረጃ አግኝቶ አይደለም፡፡ ይህ ደግሞ እንኳን ለተቃውሞ የቆመ ድርጅትን ቀርቶ ማንም ከተለያዩ ድረ ገጽ ላይ ወስዶ ራሱ በፈለገው ቅርፅና አመለካከት ቀይሮ ሊያቀርበው ይችላል፡፡ የእኔን ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም መጣጥፍ እንደፈለጋቸው የሚያደርጉ ናቸው፤” ብሏል፡፡ 

የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ በተሳሳተ ሁኔታ እየተተረጐመ መሆኑን የጠቆመው ጋዜጠኛ እስክንድር፣ ሌላው የተከሰሰበት ወንጀል የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉን አንቀጽ 23 ተላልፏል በሚል መሆኑን ተናግሯል፡፡ ዓላማውም እንደ ዓረብ አገሮች የመንግሥትን ሥልጣን በኃይል ለመያዝ መሆኑን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ማስረዳቱን የገለጸው ጋዜጠኛው፣ በዓረብ አገሮች ማለትም በግብፅ፣ በቱኒዝያ፣ በሊቢያ፣ በየመንና በሶሪያ የተደረገው አመፅ ዓቃቤ ሕግ ከሚለው በእጅጉ የተለየ መሆኑን አስረድቷል፡፡ “የሥር ፍርድ ቤት በኃይል ሥልጣን ለመያዝ የዓረብ አገሮች የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ዓላማ መከተልህ ትክክል አይደለም” በማለት ፈርዶብኛል፡፡ እኔ በፖለቲካ ድርጅት ተመርቼ ያደረግኩት እንቅስቃሴ የለም፡፡ ለአገሬ ይጠቅማል ብዬ ስላመንኩና አሁንም ስለማምን፣ ሕገ መንግሥቱን የተከተለ ዓላማ ነው ያለኝ፡፡ በዓረብ አገሮች የተደረጉ አመፆች በፖለቲካ ድርጅት የታገዙ አይደሉም፡፡ የታገሉት ወይም እየታገሉት ያለው ለነፃነትና ለፍትሕ ነው፡፡ ይህንንም ድርጊታቸውን የአፍሪካ ኅብረት ሙሉ ዕውቅና ሰጥቶታል፡፡ ይህ ድርጊታቸው እንደ ምሳሌ እንጂ እንደ ተቃውሞ ሊወሰድ አይገባም፡፡ አድርገሃል ስለተባልኩት ነገር ሁሉ አንድ ማስረጃ ከተገኘ ጥያቄዬን አነሳለሁ፤” ብሏል፡፡ በግልጽ ያደረጋቸው ቃለ ምልልሶች፣ በአንድነት ፓርቲ ላይ ንግግር እንዲያደርግ ተጋብዞ ያደረጋቸው ንግግሮችና በተለያዩ ጋዜጦችና ድረ ገጾች ላይ በግልጽ የጻፋቸውን መጣጥፎች፣ ዓቃቤ ሕግ በማስረጃነት ከማቅረቡ ውጭ ምንም ዓይነት የተደበቀና ሚስጥር ነው የተባለ ማስረጃ እንዳላቀረበበት ጋዜጠኛ እስክንድር አስረድቷል፡፡ 


የአንዱዓለም አራጌ፣ የናትናኤል መኮንንና የክንፈሚካኤል አበበ ጠበቃ አቶ ደርበው ተመስገን በበኩላቸው ባቀረቡት የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ መቃወሚያ ላይ እንደገለጹት፣ ደንበኞቻቸው የተቀጡባቸው የወንጀል ድርጊቶች እንደ ሕጉ አገላለጽ የሽብርተኝነት ወይም የአገር ክህደት ወንጀል ድርጊቶች ወይም ሙከራዎች ሊባሉ የሚችሉ አይደሉም፡፡ በማስረጃም አልተረጋገጠባቸውም፡፡ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከግንቦት 7 ጋር ግንኙነት በማድረግ የአመፅ ተግባር ለመፈጸም ያሴሩ እንደነበር፣ የኤርትራ መንግሥት በኢትዮጵያ የሚያራምደውን የሽብርና የትርምስ አጀንዳ ለማስፈጸም ከግንቦት 7 ጋር በመቀናጀት አባላትን በመመልመል ወደ ኤርትራ በመላክ፣ ወታደራዊ ሥልጠና እንዲወስዱ ያደርጉ እንደነበር በመግለጽ፣ ዓቃቤ ሕግ በደንበኞቻቸው ላይ ክስ መመሥረቱን አቶ ደርበው አስታውሰዋል፡፡ ደንበኞቻቸው የተፈረደባቸው የሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 4 እና 3 ሥር ያለውን በመጥቀስ መሆኑንም በድጋሚ አስታውሰዋል፡፡ 

ዓቃቤ ሕግ በመሠረተውና በጠቀሰው የፀረ ሽብርተኝነት ሕግ፣ የሽብርተኝነት ወንጀል ድርጊት ተፈጽሟል ሊባል የሚችለው፣ ሰው ሲሞት ወይም ከፍተኛ የአካል ጉዳት ሲደርስ፣ የኅብረተሰቡን ደኅንነትና ጤና ለከፍተኛ አደጋ ሲያጋልጥ፣ እገታ ወይም ጠለፋ ሲፈጸም፣ በንብረት ላይ ጉዳት ሲደርስ፣ በተፈጥሮ ሀብት፣ በአካባቢ፣ በታሪካዊ ወይም በባህል ቅርስ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሲደርስ፣ ማንኛውም የሕዝብ አገልግሎት ለከፍተኛ አደጋ ያጋለጠ፣ የያዘ፣ በቁጥጥር ሥር ያደረገ፣ ያቋረጠና ያበላሸ ከሆነና የዛተ ሲሆን ብቻ መሆኑ በሕጉ ተደንግጐ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡ ደንበኞቻቸው ግን ከፍተኛ ቅጣት የተጣለባቸው ስለተከሰሱ እንጂ አንድም ማስረጃ ተገኝቶባቸው እንዳልሆነ በማስረጃነት ተከራክረዋል፡፡

የሥር ፍርድ ቤት ያቀረቡትን የመከላከያ ምስክሮችና የሰነድ ማስረጃዎች በአግባቡ እንዳልመዘነላቸው የገለጹት ጠበቃው፣ ባልተጠቀሰ ክስና ባልተመዘነ የመከላከያ ማስረጃ፣ የሥር ፍርድ ቤት የሰጠውን ከፍተኛ የቅጣት ውሳኔ ፍርድ ቤቱ እንዲያይላቸው ጠይቀዋል፡፡ ከአሸባሪ ቡድን ጋር ተገናኝተዋል የሚል ክስ ቢቀርብም ከማንም ጋር ስለመገናኘታቸው የቀረበ ማስረጃ አለመኖሩንም አቶ ደርበው ተናግረዋል፡፡ ፋሲል የኔዓለም ከሚባል አሸባሪ ጋር ተገናኝቷል ለማለት መሞከሩን የገለጹት ጠበቃው፣ ፋሲል የኔዓለም ኢሳት ለሚባለው ሚዲያ ጋዜጠኛ ከመሆኑ ባለፈ የቀረበ ማስረጃ አለመኖሩንም ተናግረዋል፡፡ ኢሳትም የመገናኛ ብዙኃን እንጂ የአሸባሪ ድርጅት ሚዲያ አለመሆኑን ማረጋገጣቸውን አቶ ደርበው ገልጸዋል፡፡ 

ከኤርትራ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ተገናኝተው ማሴራቸውን በመግለጽ አገር ከድተዋል በሚል ዓቃቤ ሕግ ክስ ቢያቀርብም፣ አንድም ማስረጃ አለማቅረቡን አቶ ደርበው ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ዓቃቤ ሕግ ከጥርጣሬ ውጭ በሆነ ማስረጃ ስላላረጋገጠላቸው፣ ፈጽመዋል በሚል ያቀረበባቸውም ክስ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 68 (ሐ) መሠረት እንደ ወንጀል አይቆጠርም፡፡ የሕግ ወሰን አልፈዋል እንኳን ቢባል ጥፋተኛ ሊባሉና ሊቀጡ የሚገባው በመገናኛ ብዙኃንና መረጃ ሕግ እንጂ በፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ ሊሆን እንደማይገባው አስረድተዋል፡፡ 


ዓቃቤ ሕግ በበኩሉ ባቀረበው መከራከሪያ “የተፈጸመ የሽብር ተግባር አለ ብለን ክስ አላቀረብንም” ካለ በኋላ፣ ይግባኝ ባዮቹ በሥር ፍርድ ቤት ያቀረበባቸውን የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች መከላከል ባለመቻላቸው እንደተወሰነባቸው አስረድቷል፡፡ ይግባኝ ባዮቹ ከአሸባሪዎች ጋር ስለመገናኘታቸው የቀረበባቸው ማስረጃ የለም ስለተባለው ዓቃቤ ሕግ ሲያስረዳ፣ የትኞቹ ይግባኝ ባዮች አልተገናኙም እንደተባለ ስላልተገለጸ ምላሽ መስጠት እንደማይችል ተናግሯል፡፡ ማስረጃ አልቀረበባቸውም የተባለው በድብቅ ይገናኙ ስለነበር መሆኑን፣ ኢሳት የመገናኛ ብዙኃን ነው ቢባልም ለግንቦት 7 ወግኖ ወይም አድልቶ የሚሠራ መሆኑን በመግለጽ አንድ ሠራተኛ መልቀቂያ አስገብተው መልቀቃቸውን በማስረጃነት ማቅረቡን፣ መረጃ መለዋወጥ እንጂ ወንጀል አልተፈጸመም ማለት እንደማይቻል ዓቃቤ ሕግ አስረድቷል፡፡ ሁሉም ግንኙነት እንዳላቸው የሚያስረዳ ማስረጃ ማቅረቡንም ተናግሯል፡፡ ወረቀት ሲበተን እንደነበርና ሌሎች ማስረጃዎችንም ማቅረቡን የዓቃቤ ሕግ ገልጿል፡፡

የሰሜን አፍሪካ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ አይፈጸምም ሊባል እንደማይቻልና ከአሸባሪ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት አልተደረገም መባሉን እንደሚቃወም የገለጸው ዓቃቤ ሕግ፣ አቶ እስክንድር የግንቦት 7 አባል ለመሆናቸው የሰው ምስክር ማቅረቡን ለአብነት ገልጿል፡፡ ሌላው ዓቃቤ ሕግ ያነሳው መከራከሪያ ነጥብ፣ ጋዜጠኛ እስክንድር የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚያማክርበት ምክንያት እንደሌለና አግባብ እንዳልሆነ ነው፡፡ በአገር ውስጥ ስለሚደረገው እንቅስቃሴም በግንቦት 7 ድምፅ ላይ ተጽፎ ማግኘቱን “ነፃ የኢትዮጵያ ትውልድ ኮሚቴ” የሚል ሲቪክ ማኅበር አቋቁመው በሽፋንነት ሲሠሩበት እንደነበርና ቀስቃሽና ወደ አመፅ ሊያመራ የሚችል ጽሑፍና ንግግር ማቅረባቸውንም አስረድቷል፡፡ 

ጋዜጠኛ እስክንድር በክርክር ማጠናቀቂያ መልሱ ላይ እንደገለጸው፣ የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ ሕገ መንግሥታዊ መብቱን የሚጥስ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ያደረገቻቸው ምርጫዎች የሉም ሳይሆን ሕገ መንግሥቱን የጣሰና ነፃ አይደለም፡፡ የግንቦት 7 አባል የተባለው ደግሞ ከአበበ በለው ጋር ቃለ ምልልስ ስላደረገ ነው፡፡ አበበ ደግሞ ጋዜጠኛ ነው፡፡ ጓደኛውም ነው፡፡ የግንቦት 7 አባል እንዳልሆነና ያደረገውም ቃለ ምልልስ በመገናኛ ብዙኃን መተላለፉን አስታውቋል፡፡ 

አቶ ደርበውም በክርክር ማቆሚያቸው እንደገለጹት፣ ደንበኞቻቸው በግፍ መታሰራቸውንና የታሰሩትም ማስረጃ ባልቀረበበት ሁኔታ ክስ ስለቀረበ ብቻ ነው፡፡ ይህንን ካስረዱ በኋላ “ሕገ መንግሥቱ ግን እንዴት ነው የሚከበረው?” በማለት ንግግራቸውን በጥያቄ አቁመዋል፡፡ 

ሌላው ለፍርድ ቤቱ ቅሬታ ያቀረበው  አቶ አንዱዓለም አራጌ ሲሆን፣ ለአንድ ዓመት ከሦስት ወር መሬት ላይ እንዲተኛ መደረጉን፣ አልጋ እንደተከለከለ፣ ትንሽ ብርሃን ባለበት በጨለማ ክፍል ውስጥ ከስድስት ሰዎች ጋር መታሰሩን፣ የመተንፈስ ችግር እንዳለበት፣ ከተወሰኑ ቤተሰቦቹ በስተቀር ሌላ ሰው እንዳይጠይቀው መከልከሉን አስረድቷል፡፡ ጠበቆቹም ከደንበኞቻቸው ጋር መገናኘት እንዳልቻሉ ምክንያቱ ደግሞ የተወሰኑት ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ሲሆኑ የተወሰኑት ቃሊቲ ማረሚያ ቤት በመሆናቸው ነው፡፡ 

ፍርድ ቤቱ ግራ ቀኙን ከሰማ በኋላ በቅሬታዎቻቸው ላይ ትዕዛዝ እንደሚሰጥበት ገልጿል፡፡ ጋዜጠኛ እስክንድር ጋዜጠኛ መሆኑን ገልጾ የሚሠራበት ጋዜጣን ስም ሲጠይቀው “በአገሬ ላይ እንዳልሠራ መንግሥት በሕገወጥ መንገድ ከልክሎኛል” ካለ በኋላ፣ በኢትዮ ሚዲያ፣ በአዲስ ቮይስና በሌሎችም ድረ ገጾች ላይ እንደሚጽፍ ተናግሯል፡፡ ንግግሩ ስሜት የተሞላበት ስለነበር ፍርድ ቤቱ “በፊት ደህና ተከራክረው ነበር፣ ስሜት ውስጥ መግባት አያስፈልግም፤” በማለት ውሳኔ ለመስጠት ለጥር 10 ቀን 2005 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቶ ችሎቱ አብቅቷል፡፡  
 Sourace <reporter Amaric

4 comments: