Monday, December 10, 2012

የታህሳስ ግርግር ሊደገም ይሆን?

የታህሳስ ግርግር ሊደገም ይሆን?     

                                                             
By Temesgen Desalegn

መነሻ ታሪክ
ለዘመናት በኢትዮጵያውያን ጫንቃ ላይ በመጣበቅ ‹‹ቫምፓየር›› ሆኖ የነበረው የአጼ ኃይለስላሴ አገዛዝ አጥንት ድረስ ዘልቆ የሚሰማ ቁጭትና ኃዘኔታ የፈጠረባቸው ጥቂት ሰዎች ነበሩ፡፡ ግርማሜ ነዋይና አባሪዎቹ፡፡ 
ከሀገሪቱ ህዝብ ከ85 በመቶ በላይ የሚሆነው ‹‹አፈር ገፍቶ›› አዳሪ ቢሆንም፣ ጉልተኛው ስርዓት የወዙን ሲሶ ብቻ እንዲያገኝ ነበርና የተፈቀደለት፣ ከዓመት ዓመት በረሃብ እንዳለቀ፣ ጎጆው ከኃዘን ጋር ጋብቻ እንደፈፀመ፣ ህፃናት ልጆቹ ጠግበው ሳይበሉ፣

 እንደ ልጅ ሳይቦርቁ በልጅነታቸው ዳግም ወደ ማይመለሱበት ዓለም መሄዳቸው ከማንም በላይ ያንገበገበው በሀገረ አሜሪካ እስከ ሁለተኛ ዲግሪው ድረስ የተማረው ግርማሜ ነዋይ፣ በወቅቱ በብርጋዴል ጄነራል ማዕረግ የአፄው ስርዓት ዋነኛ ጠባቂ የነበረው የ‹‹ክብር ዘበኛ›› አዛዥ ከነበረው ታላቅ ወንድሙ መንግስቱ ንዋይ፣ የፖሊስ አዛዡ ጄነራል ፅጌ ዲቡ፣ የፀጥታ ኃላፊው ኮለኔል ወርቅነህ ገበየው እና ጥቂት ቆራጦች ያላቸውን ኃይል አስተባብረው፣ ዘራፊውን ዘውዳዊ ስርዓት በኃይል ለማስወገድ ታህሳስ 2 ቀን 1953 ዓ.ም የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ አደረጉ፡፡ ሆኖም ሙከራው በብዙ መስዕዋትነት ቢቀለበስም፣ የለውጡን መንፈስና ይዘውት የተነሱትን ጥያቄ ግን መቀልበስ አልተቻለምና፤ ይህ ከሆነ ከ13 ዓመት በኋላ የንጉሱ ስርዓት ላይመለስ በሕዝብ ኃይል ተሰናበተ፡፡ …የእነ ግርማሜ ነዋይ ሕዝባዊ ትግል የተቀሰቀሰበት ያ ዕለትም በሀገሪቱ ታሪክ ‹‹የታህሳስ ግርግር›› በመባል በወርቅ መዝገብ ተጻፈ፡፡
ታሪክ ሊደገም ይሆን?
እነሆም በስምና በጥቂት ነገሮች ከ“ቫምፓየሩ" የአጼው ስርአት መጠነኛ ለውጥ አድርጎ ወደ ስልጣን የመጣው ኢህአዴግ መራሹ መንግስት የዲሞክራሲና የፍትሕ ጥያቄ ያነሱ ጋዜጠኞችንና ፖለቲከኞችን በዛሬው ዕለት (ታህሳስ ሁለት ቀን) ፍርድ ቤት ያቀርባል፡፡ በዚህም መሰረት ርዕዮት አለሙ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የኦፌዴንና የኦህኮ የአመራር አባላት ኦልባና ሌሊሳ እና በቀለ ገርባን ጨምሮ 29 ሰዎች በከፍተኛው ፍርድ ቤት ፣ እኔ ደግሞ በነሃሴ ወር ተቋርጦ ከቃሊቲ በነፃ በተለቀኩበት ክስ በድጋሚ በከፍተኛው ፍርድ ቤት 16ኛ ወንጀል ችሎት እንቀርብ ዘንድ ተገደናል፡፡ የታህሳስ ግርግር መንፈስ ማለትም ይህ መሰለኝ፡፡
የሆነ ሆኖ ይህ ሁሉ ንፁሐን ጋዜጠኛና ፖለቲከኛ ፍርድ ቤት የሚቀርበው የሀገሬ ጉዳይ ይመለከተኛል በሚል የመብትና የዲሞክራሲ ጥያቄ በማንሳቱ ነው፡፡ በእርግጥም በግሌ ትላንት ያነሳሁትን ጥያቄ ነገም እንደማነሳው ቃል እገባለሁ፡፡ አምኜበት እና እውነትነቱን አረጋግጬ በፍትሕ ጋዜጣ በኩል ላስተላለፍኳቸው ሃሳቦች ዋጋ መክፈል ካለብኝ ዋጋ እከፍላለሁ እንጂ የትም ልሄድ አልችልም፡፡ እናም ፍርድ ቤቱ በሀቅ የሚሰጠውን ውሳኔ በደስታ እንደምቀበለው ሁሉ፤ በትዕዛዝ የሚፈርድብኝንም የግፍ ፍርድ በፀጋ እቀበለዋለሁ፡፡
ጭቆና፣ የመብት ረገጣ፣ አምባገነን አገዛዝ፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት፣ የሀገር ሃብት ዘረፋ፣ አድሎአዊ አስተዳደር… እስካልተወገደ ድረስ እኔም ሆንኩ ሌሎች የጠየቅነውን ጥያቄ ሚሊዮኖች እንደሚጠይቁት አምናለሁ፡፡ በዚህ ላይ ባለኝ እምነትም ነገ በፍርድ ቤት የምገኘው የቅርብ ጊዜን ተስፋ ሰንቄ ነው፡፡ በጣም የቅርብ ጊዜ፡፡ ድምፄን ከፍ አድርጌ እንዲህም እላለሁ ፤ በጣም ከፍ አድርጌ፣ ይታየኛል የሀገሬ ልጆች፣ ሴቶችና ወንዶች እጅ ለእጅ ተያይዘው ዳገቱ ላይ ሲደርሱ፡፡
ኢትዮጵያ ለዘላለም



No comments:

Post a Comment