Sunday, December 29, 2013

ፍትህ የተጠማች ብላቴና


ፍትህ የተጠማች

አሳዛኝ ግፍ የስምንት አመቷ ስለእናት ማስረሻ ቀኝ እጇ ላይ በጥይት ተመታች፡፡ባለቤታቸውን በሞት የተነጠቁትና ምንም የማታውቀውን ህጻን ልጃቸውን አካለ ጎደሎ ያደረገባቸውን ጥይት ማን እንደተኮሰው ለማወቅ ለዳባት ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ አቤት ሲሉ ‹‹ባለቤትዎ ሽፍታ እንደሆኑ መረጃ ስለደረሰን ግድያውን የፈጸመው የጸረ ሽብር ግብር ሃይል ነው››ተብለዋል፡፡ ‹‹ሽፍታ እንዴት ባለ80 ቆርቆሮ ቤት ይሰራል? ልጆቹን ያስተምራል? ሞዴል አርሶ አደር ተብሎ ይሸለለማል? በየት አገር በብአዴን ስብሰባ ላይ እንድትገኝ ተብሎ በደብዳቤ ይጠራል? እንዴት ሽፍታ የመለስ ዜናዊን አደራ ለመወጣት በምንችልበት ሁኔታ ለመወያያት እንድንነጋገር ይባላል? ›› ጥያቄዎቹን ፖሊሶቹ ሊመልሱላቸው ባለመቻላቸው ወደ ክልሉ አስተዳደር አምርተዋል፡፡ክልሉ ለዞኑ ዞኑ ለወረዳው ደብዳቤ እየጻፈ እስካሁን ድረስ የአቶ ማስረሻ እውነተኛ የግድያ መንስኤ መታወቅ አልቻለም፡፡ ይህች ህጻንና ቤተሰቦቿ የሁላችሁንም ወገንተኝነት በአክብሮት ይጠይቃሉ ሰሜን ጎንደር ዳባት ወረዳ ነዋሪ የነበሩት የ55 ዓመቱ አቶ ማስረሻ ጥላሁን የተመሰከረላቸው አርሶ አደር ገበሬ በመሆናቸው የክልሉ ግብርና ጽ/ቤት ሞዴል አርሶ አደር በማለት ሸልሟቸዋል፡፡የሁለት ወንድና የአምስት ሴት ልጆች አባት የሆኑት አቶ ማስረሻ ወሰኔን ገፍተሃል የሚል ክስ ቀርቦባቸው በዳባት ፍርድ ቤት 300 ብር መቀጮ ተጥሎባቸው በመክፈል ወደ እርሻቸው ቢመለሱም የገበሬ ቀበሌ ማህበሩ ሊያስቀምጣቸው አልቻለም፡፡ ጥቅምት 15/2006ዓ.ም ከሁለተኛ ልጃቸው ሰለሞን ማስረሻ ጋር አትክልት ተክለው አመሻሹ ለይ ተዳክመው መኖሪያ ቤታቸው ገብተዋል፡፡ማለዳ 12፡00 ከመኝታው ባላቋረጠው የውሾች ጩህት ከእንቅልፉ ተነሳው ሰለሞን በሩን ከፍቶ ሲወጣ የጥይት እሩምታ ይወርድበታል፡፡አባት ልጄን ብለው የሌሊት ልብሳቸውን እንደለበሱ ወደ ውጪ ሲወጡ የጥይቶቹ አቅጣጫ ወደ እርሳቸው በመዞሩ ማን እንደተኮሰባቸውና ማን እንደመታቸው ለማየት እንኳን ሳይታደሉ ይህችን ጨካኝ አለም ተሰናበቱ፡፡ መኖሪያ ቤቱ ላይ በሚወርደው የጥይት እሩምታ የተነሳ ሁለት ላሞችና አንዲት ጊደር ተገደሉ፡፡የስምንት አመቷ ስለእናት ማስረሻ ቀኝ እጇ ላይ በጥይት ተመታች፡፡



Tuesday, December 24, 2013

የሰው ህይወት ከዱር እንሰሳ ያነሰበት!!!!

>>>የሰው ህይወት ከዱር እንሰሳ ያነሰበት!


ኣብዛኞቹ ኦሮሞ የሆኑ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰብ ተወላጆች ባገራቸው ሰርተው ማደግ ተስኖኣቸው በያመቱ ወደ ጎርቤትና ሩቅ ሃገራት ይሰደዳሉ። ኣብዛኞቹ በህገ ወጥ መንገድ ድንበር ኣሳብረው ጎሮቤት ኣገራት ይገባሉ። ጎሮቤት ኣገራቱ ውስጥም የወያኔ መንግስት ተጽእኖ ኣላሰራ ሲላቸው ለደህንነታቸው ሰግተው ርቀው ለመሄድ ሲሉ የከፋ ኣደጋ ያጋጥማቸዋል። በዚህ ሁኔታ በሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ሶማሊ ላንድ፣ ፑንት ላንድ፣ ጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ የመን፣ ሳውዲ ኣረቢያ፣ ዱባይ፣ ባህሬን፣ ሊባኖስ፣ ቃታር፣ ግብጽ እና ደቡብ ኣፍሪካ በመሳሰሉት ኣገራት ውስጥ ተሰድደው የሚገኙ ከኦሮሞና ከሌሎችም ብሄር ብሄረሰብ የሆኑ ዜጎች ብዛት በመቶ ሺዎች የሚገመት ነው።
ከነዚህ ስደተኞች አብዛኞቻችን በፖለቲካ ችግር ሳቢያ የሚወዷትን ኣገራቸውን ለቀው የወጡ ናቸው። የተቀሩትም ባገራቸው ሰርተው የመለወጥና ራሳቸውን ችለው ቤተሰቦቻቸውን የመደገፍ እድል ተነፍገው በፖለቲካ ኣመለከከታቸዉ አነ በዘረቸው ምከነያት በደረሰበቸው ግፉ ርቀው የሄዱ ናቸው። ባገራቸው ነግደው፣ ኣርሰው፣ ኣርብተው ኣልያም ባላቸው ሞያ ኣገልግለው እንዳይለወጡ ስልጣን ላይ ያለው ስርኣት እንቅፋት ሆነባቸው። የወያኔ መንግስት ባገራቸው ከማናቸውም መንግስታዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ነጻ ሆነው ሰርተው መሻሻል የሚፈልጉትን ዜጎች የግድ የፓርቲዬ ኣባል ካልሆናችሁ እያለ ያስፈራራቸዋል። ይህን የማይቀበሉትን በሰበብ ኣስባቡ ኣደናቅፎ የስራ እድል ይዘጋባቸዋል። ኣርሶ ኣደሮቹን የማዳበሪያና የምርጥ ዘር ዋጋ ያስወድድባቸዋል ኣልያም ከናካቴው ይከለክላቸዋል። ነጋዴዎቹን ውሃ ቀጠነ ብሎ በማስቸገር የንግድ ፈቃዳቸውን ከነጠቀ በሁዋላ ይህን ያህል ሺ ገንዘብ ካልከፈልክ ኣታገኝም ይላቸዋል። ወደ ንግዱ ኣለም ለመግባት ያላቸውን ሃብት ኣስይዘው ከባንክ ገንዘብ መበደር የሚፈልጉትን በቅድሚያ የፓርቲያችን ኣባልነት መታወቂያ ኣምጣ በማለት ያሰናክላቸዋል። እነዚህ እንቅፋቶች ዜጎች ባገራቸው ሰርተው ራሳቸውንም ሆነ ኣገራቸውን እንዳያሳድጉ በማደናቀፍ ልባቸው ስደት እንዲመኝ ገፋፉ። ከኢትዮጵያ እየወጡ ወደተለያዩ ኣገራት ስራ ፍለጋ የተሰደዱ ዜጎች ቁጥር ከማናቸውም የጎሮቤቶቻችን ኣገሮች ልቆ የሚገኝበት ምክንያትም በዚህ ኣይነቱ የመንግስት ተጽእኖ ሳቢያ ነው ቢባል ማጋነን ኣይሆንም።
እነዚህ ስራ ፍለጋ የሚንከራተቱ ዜጎች የኢትዮጵያ ዜጎች እስከተባሉ ድረስ በደረሱበት ሁሉ ደህንነታቸውን የመከታተል ሃላፊነት የወደቀው ኣገር መሪ ነኝ በሚለው የወያኔ መንግስት ጫንቃ ላይ ነው። የወያኔ ህወሃት መንግስት ግን በኣንጻሩ ስደተኞቹ በደረሱባቸው ኣገራት ለሰብኣዊ ፍጡር የማይገቡ የጭካኔ እርምጃዎች ሰለባ እንዲሆኑ በማድረጉ ሴራ ውስጥ በቀጥታም ባይሆን በተዘዋዋሪ ተሳታፊ መሆንን መረጠ። በተለያዩ ጊዜያት ዜጎች ለስራ ፍላጋ በተሰደዱባቸው ኣገራት ተገድለው ሬሳቸው ጎዳና ላይ ሲጣል፣ ደማቸው እንደ ውሻ ደም የትም ሲፈስ ወያኔ ይህ ለምን ሆነ ብሎ ሲጠይቅ ኣልተሰማም።
ሰርተው ለመቀየር ያለሙ የኣገራችን ሴቶች ለግርድና ስራ ወደ ኣረብ ኣገራት ተሰድደው በጭካኔ ሲገደሉ፣ ሲደፈሩና ያፈሩትን ጥሪት ሲነጠቁ በተደጋጋሚ ተሰምቷል። ኣንዳንዶቹ ምሬት ጠንቶባቸው ከፎቅ ላይ ራሳቸውን ወርዉረው ነፍሳቸውን እንዳጠፉም ይታወቃል። ከኣንድ ኣመት ገደማ በፊት ኣለም ደቻሳ የተባለች የኦሮሞ ተወላጅ በቤይሩት ጎዳና ላይ በኣገሬው ሰዎች እንደ እባብ ስትቀጠቀጥ የሚያሳይ ቪድዮ በ ዮቲዩብ መለቀቁ ይታወሳል። ኣለም በወቅቱ እነዚያ ኣረመኔ የኣረብ ወጣቶች የሴትነት ክብሯን ደፍረው እርቃኗን ጎዳና ለጎዳና እየጎተቱ ሲጫወቱባት እዚያ ኣገር የሚገኘው የወያኔ ኤምባሲ እንዲደርስላት እያለቀሰች ስትማፀን በዚያው ቪድዮ ላይ ተስምታለች። ኤምባሲው ግን ኣልደረሰላትም። የሚገርመው ደግሞ ኣለም ደቻሳ ላይ እንዲህ ያለው ዘግናኝ በደል የደረሰው የወያኔ ኤምባሲ ካለበት ሁለት መቶ ሜትሮች ብቻ ርቆ በሚገኝ ስፍራ ላይ መሆኑ ነው። የወያኔ መንግስት በዚህ ኣንገብጋቢ ጉዳይ ላይ የኣገሪቷን መንግስት የጠየቀው ነገር ኣልተሰማም።
በቅርቡም እንደሚታወቀው ሳዉዲ ኣረቢያ ውስጥ በስራ ላይ ተሰማርተው ይኖሩ በነበሩ የኢትዮጵያ ዜጎች ላይ ኣስነዋሪ የጭካኔ እርምጃዎች ለሳምንታት ሳይቁዋረጡ እየተወሰዱ ናቸው። በዚህም እርምጃ ቢያንስ የሶስት ዜጎች ህይወት ጠፍቷል። የሳውዲ ፖሊሶች ከኣገሬው ወጣቶች ጋር በመሆን ዜግነታቸው ከኢትዮጵያ በሆነ ስድተኞች ላይ የተለየ ኣስነዋሪ የጭካኔ ድርጊት ሲፈጽሙ በተቀረጸው የቪድዮ ምስል ታይተዋል። ይህ ሁሉ ሲሆን እነዚህ የሚደበደቡ፣ የሚገደሉና የሚደፈሩ ዜጎች የትውልድ ኣገር መንግስት የሆነው ወያኔ ኣፉን ሞልቶ ድርጊቱን ሲያወግዝ ኣልተሰማም።
እንደ ኢንዶኔዢያና ፊሊፒንስ ያሉ መንግስታት ዜጎቻቸው ከሳውዲ በሃይል መፈናቀላቸውን ተቃውመው ወዲያውኑ የቅሬታ መግለጫ በማውጣት የሳውዲን መንግስት ኣወገዙ። በሳውዲ የሚኖሩትን የሃገራቸው ስደተኛ ዜጎች ደህንነት ለማስጠበቅ ባላቸው ኣቅም ሁሉ እርምጃ ወሰዱ። የወያኔ መንግስት ግን እንዲህ ያለውን መንግስታዊ ሃላፊነት መወጣት ቀርቶ እንዲያውም የሳውዲን መንግስት ጸረ ሰብኣዊ መብት እርምጃ ለመደገፍ እየተሞዳሞደ መሆኑን በራሱ ላይ መስከረ። በኣገሩ ዜጎች ላይ ሳውዲ ውስጥ እየደረሰ ላለውና ኣለምን እያሳዘነ ለሚገኘው ውርደት ስሜት ኣልነበረውም። ወያኔ ዘንድ ዋጋ የሚያወጣው ለኣገሩ ዜጎች ክብር መቆም ሳይሆን ለሳውዲ ኢንቨስተሮች መሬት ሸጦ ኣልያም በነጻ ሸንሽኖ እየሰጣቸው በኣጸፋው በሚወረወርለት ጥቅማ ጥቅም የንዋይ ጥማቱን ማርካት ብቻ ነው። ዜጎች ኣገራቸው ላይ ሰርተው እንዳያድጉ በሰበብ ኣስባቡ ገፍቶ በማስወጣት እነርሱ ለቀው የሄዱለትን መሬት ዛሬ ዜጎቹን እየገደሉ ላሉት የኣረብ ጥጋበኞች ይቸበችባል። ይህ የኣንድ ጸረ ህዝብ መንግስት ትልቁ መለያ ምልክት ነው።
እንደ ሱዳን፣ የመን፣ ጅቡቲ፣ ሶማሊ ላንድ፣ ፑንት ላንድ፣ ኬንያና በመሳሰሉት ሃገራት ውስጥ ከረጅም ጊዜ በፊት ጀምሮ ከኢትዮጵያ በሄዱ ዜጎች ላይ የሚደርሰው የሞትና እንግልት ኣደጋ ተነግሮ የሚያልቅ ኣይደለም። ይህ ሁሉ ሲሆን ታዲያ የወያኔ መንግስት ከነዚያ የባእድ መንግስታት ጋር ተባብሮ ስደተኞቹን ማስገደል፣ ማሳሰርና ወደ ሃገር ቤት መልሶ ማሰቃየት ካልሆነ በስተቀር ዜጎቼ ብሎ ደርሶላቸው ኣያውቅም።
በጥቅሉ ሲታይ በባእድ ኣገራት ውስጥ በኦሮሞና ሌሎችም ብሄር ተወላጅ ስራ ፈላጊ ስደተኞች ላይ እየደረሰ ላለው ሰቆቃ ዋነኛ ተጠያቂው ባእዳኑ መንግስታት ሳይሆኑ ራሱ የወያኔ መንግስት ነው። በበርካታ ምክንያቶች ተጠያቂ ይሆናል። በመጀመሪያ ደረጃ ስደተኞቹን ገፍቶ ከሃገር እንዲወጡ በማድረጉ ይጠየቃል። በሁለተኛ ደረጃ ስደተኞቹ በደረሱባቸው ኣገራት ሰብኣዊ መብታቸው ተከብሮ እንዲሰሩ በኤምባሲዎቹ ኣማካኝነት ክትትል ባለማድረጉ ተጠያቂ ይሆናል። ሶስተኛ ደግሞ ስደተኞቹ በሚኖሩባቸው ኣገራት ሰብኣዊ መብቶቻቸውን ሲገፈፉ ፈጥኖ ደርሶላቸው ተገቢውን እርምጃ ኣለመውሰዱ ተጠያቂ ያደርገዋል።
ከሁሉም በላይ ግን ስራ ፈላጊዎቹ ዜጎች በገዛ ኣገራቸው ላይ ሰርተው ራሳቸውን እንዲችሉ በማበረታታት ምትክ ተስፋ ቆርጠው ስደትን እንዲመርጡ መገፋፋቱ ትልቅ መንግስታዊ ጉድለት ነው። ዜጎቹ ኣገራቸውን ለቀው ኣንዳይሄዱ ለማድረግ ከፖለቲካ ተጽእኖ ነጻ የሆነ የስራ እድል ማመቻቸት መንግስታዊ ሃላፊነቱ ነበረ። ሁሉም ዜጎች በሚኖሩባቸው ክልሎች ከማናቸውም የፖለቲካ ኣመለካከቶች ነጻ የሆነ ሰርቶ የመሻሻል እድል ማግኘት መብታቸው ነበር። ወያኔ ያንን የዜግነት መብታቸውን ቀማ። ለምሳሌ የኦሮሞ ተወላጆች በክልላቸው ኦሮምያ ውስጥ ባለው የተፈጥሮ ሃብት ተጠቅመው ሰርተው መሻሻል ይችሉ ነበር። በእርሻ፣ በከብት ርቢ፣ በንግድ እንዲሁም በሲቪል ኣገልግሎቶች መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ መዋቅሮች ውስጥ ያላንዳች የፖለቲካ ተጽእኖ ተሰማርተው ራሳቸውንም ሆነ ኣገራቸውን መጥቀም ይችሉ ነበር። የወያኔ መንግስት ግን እነዚህን መሰል የስራ እድሎች ነጥቆኣቸው ለስደት ህይወት ዳረጋቸው። በስመ እንቬስተርነት የራሱን ካድሬዎችና ሰላዮች መልምሎ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ኣሸክሞ ክልሎች ላይ በማሰማራት የስራ እድሉን ነጠቃቸው።
የዚህ ችግር መንስኤ ራሱ የወያኔ መንግስት ኣድሎኣዊ ኣሰራር እስከሆነ ድረስ የችግሩ መፍትሄም በራስ ኣገር ላይ ሰርቶ የመኖርን መብት የቀማውን ስርኣት ታግሎ የራስን መብት ማስከበር ብቻ ነው። የነዚህ ስራ ፈላጊ ስደተኞች ችግር ላይ ላዩን ሲታይ የኢኮኖሚ ችግር ይምሰል እንጂ መሰረቱ ግን ኣገር ቤት ላይ የሚደርሰው የፖለቲካ ጫና መሆኑ ታውቆ የፖለቲካ መፍትሄ ሊያገኝ ይገባል። ጎሮቤት ኣገራትና መካከለኛው ምስራቅ ውስጥ ስራ ፍለጋ ሲንከራተቱ የተገደሉ፣ የተደበደቡ፣ ለኣካል ጉድለት የተዳረጉ፣ የታሰሩና በሃይል ተይዘው ወደ ኣገራቸው የተመለሱ የኦሮሞና ሌሎች ብሄሮች ተወላጅ የሆኑ ዜጎች በሙሉ ራሳቸውን መጠየቅ ያለባቸው ጥያቄም ይሄው ነው። ኦሮምያ ላይ ሌላው ሰርቶ በኣጭር ጊዜ ውስጥ ሚሊዮነር ሆነ ሲባል እኔ ለምን ኣገሬ ላይ ሰርቼ ማደግ ተሳነኝ? ለምን ለስደት ህይወት ተጋልጬ በባእድ ኣገር ላይ ተዋረኩ? የሚሉትን ጥያቄዎች ራሳቸውን ጠይቀው ምላሹንም ማግኘት ይገባቸዋል።

Saturday, December 21, 2013

ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን በማሰር ከዓለም 2ኛ ሆነች!!!







መቀመጫውን በኒዮርክ ያደረገው የጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪ ቡድኑ /CPJ/  ባለፈው ረቡዕ  ይፋ ባደረገው ሪፖርት፤ ጋዜጠኞችን በማሰር ከአለም አስር አገሮች መካከል ኢትዮጵያን በሁለተኛ ደረጃ ያስቀመጠ ሲሆን ኤርትራ ቀዳሚ ሆና፣ ግብፅ በሶስተኝነት ተቀምጣለች፡፡ 
ሲፔጂ 34 አፍሪካዊ ጋዜጠኞች በሰሜንና ምስራቅ አፍሪካ በእስር ላይ እንደሚገኙ የገለፀው ሲፒጄ፤ በኢትዮጵያ ሰባት ጋዜጠኞች በጻፉት ጽሑፍ ሣይሆን “አሸባሪ” ተብለው በእስር ላይ እንደሚገኙ ጠቁሟል፡፡ 
አለም አቀፍ የመብት ቡድን (Global rights group) የተባለው ተቋም በበኩሉ፤ የኢትዮጵያ መንግስት ጋዜጠኞቹን ያሰራቸው ሚዲያውን ዝም ለማሰኘት ስለሚፈልግ ነው ብሏል። በኤርትራ 22 ጋዜጠኞች በእስር ላይ እንደሚገኙና አንዳቸውም ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡ የገለፀው ሲፒጄ፤ እስረኞቹን በተመለከተ ከኤርትራ መንግስት ምንም አይነት መረጃ ለማግኘት እንደተቸገረ ጠቁሟል፡፡ ጋዜጠኞችን በማሰር የ3ኛ ደረጃን በያዘችው ግብፅም ጋዜጠኞች መታሰር የጀመሩት ፕሬዚዳንት መሀመድ ሙርሲ ወደ ስልጣን ከመጡበት ቀን ጀምሮ ነው ብሏል ሲፒጄ፡፡ የሰሜን ምስራቅ አፍሪካ ጋዜጠኞች ተወካይ ቶም ሮዲስ በናይሮቢ ለCPJ እንደተናገረው፤ በአፍሪካ ቀንድ አገራት የተለያዩ ችግሮች እንዳሉና መንግስታት ስለ ችግሩ መወያየት እንደማይፈልጉ ገልጿል፡፡ ሲፒጄ ጋዜጠኞችን በማሰር ቀዳሚዎቹ 10 አገራት በሚል ከዘረዘራቸው መካከል ቬትናም፣ ሶሪያ፣ ፓኪስታንና ቤልጂየም ይገኙበታል፡፡

Tuesday, December 10, 2013

ዓለም ማንዴላን ተሰናበተች!








ማክሰኞ፣ ታኅሣስ 1/2006 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ በብዙ አሥር ሺሆች የተቆጠረ ህዝብ ዕኩልነትን ዕውን ለማድረግ አስቸጋሪ የሆነ የረጅም ጊዜ ትግል ያካሄዱትን የፀረ-አፓርታይድ ትግል መሪውን ኔልሰን ማንዴላን ተሰናብቷል።

በጆሐንስበርግ ሶከር ሲቲ ስታዲየም የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማንና የቀደሙ የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶችን ጨምሮ በርካታ ታላላቅ ዕንግዶች፣ ታዋቂ ሰዎች እና ደቡብ አፍሪካዊያን መጥፎ የአየር ሁኔታ ሳይበግራቸው እኒህን ሁሉ ሰው ”ታታ” እያለ በፍቅር የሚጠራቸውን ሰው በአክብሮት ለመሰናበት ተገኝተዋል

Sunday, December 8, 2013

የደህንነት አባሉ ተጨማሪ 11 ክሶች ቀረበባቸው!



<<>>>በርካታ ድርጅቶች በሽብር ላይ የሚያተኩር መጽሐፋቸውን በተጽዕኖ እንዲገዟቸው አድርገዋል
>>>>>ከቤተሰቦቻቸው ጋር በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብና ሃብት አፍርተዋል
>>>>>ሁለተኛ ተከሣሽ ደግሞ በመከላከያ ውስጥ ተቀጥሮ ሲሠራ ደሞዙ 523 ብር ሆኖ ሳለ፣ በ3 የንግድ ባንክ ቅርንጫፎች ከ150 ሺ እስከ 2 ሚሊዮን ብር ሲያንቀሳቀስ እንደነበር ተመልክቷል

ከቤተሰቦቻቸው ጋር በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብና ሃብት አፍርተዋል የቀድሞው የደህንነት አባልና የትግራይ ልማት ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ወልደስላሴ ወልደሚካኤል፤ ከቤተሰባቸው ጋር በመሆን ፈጽመውታል በተባለው የሙስና ወንጀል ተጨማሪ 11 ክስ ቀረበባቸው፡፡ ግለሰቡ ከእነ አቶ መላኩ ፈንታ ጋርም በሌላ መዝገብ መከሰሳቸው ይታወሣል፡፡ አቶ ወልደስላሴ፤ አሁን ለተጨማሪ ክስ የዳረጋቸውን ወንጀል ፈፀሙ የተባለው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት መ/ቤት ሠራተኛ በነበሩበት ጊዜ ሲሆን ከፊሉን ከወንድማቸው አቶ ዘርአይ ወ/ሚካኤል፣ ከእህታቸው ወ/ሮ ትርሃስ ወ/ሚካኤል እንዲሁም ከቅርብ ጓደኛቸው አቶ ዳሪ ከበደ ጋር በመመሳጠር፣ ከፊሉን ለብቻው እንደፈፀሙ ተገልጿል፡፡ ከትናንት በስቲያ ክሣቸው በንባብ የተሰማው አቶ ወልደስላሴ፤ በ1ኛነት የቀረበባቸው ክስ፤ የደህንነት መስሪያ ቤት ባልደረባ መሆናቸውን መከታ በማድረግ፣ በ2002 ዓ.ም “Terrorism in Ethiopia and the Horn of Africa” የተሰኘ መጽሐፋቸውን፣

ከመንግስት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ በየነ ገ/ስላሴ ጋር ያላቸውን መልካም ግንኙነት በመጠቀምና ግለሰቡን በማታለል፣ ኤጀንሲው በሚያስተዳድራቸው ብርሃንና ሠላም ማተሚያ ድርጅት፣ ቦሌ ማተሚያ ድርጅት እና አርቲስቲክ ማተሚያ ድርጅት ስፖንሰር አድራጊነት፣ 3ሺህ መጽሐፍት በ124,000 ብር እንዲታተሙ አስደርገው በመሸጥ ገንዘቡን ለግል ጥቅማቸው አውለዋል ይላል፡፡ በዚያው ክስ ላይ በ2ኛነት የቀረበው ክስ ደግሞ፤ ግለሰቡ በዚያው አመት ይህንኑ መጽሐፍ 10ሺህ ኮፒ ለማሳተም በሚል የመጽሐፉ ይዘት ከቴሌኮሙኒኬሽን ጋር ባልተገናኘበት እና የማስተዋወቅ ስራም ባልተሠራበት ሁኔታ የደህንነት አባልነታቸውን መከታ በማድረግ ከወቅቱ የቴሌኮምኒኬሽን ሃላፊ አቶ አማረ አምሣሉ ከ385ሺ ብር በላይ መቀበላቸውን ይጠቁማል፡፡

በዚሁ ክስ ላይ በ3ኛ እና በ4ኛነት በቀረቡት ክሶች፤ ግለሰቡ በኢትዮጵያ አትክልትና ፍራፍሬ ገበያ አክሲዮን ማህበር እንዲሁም በሙገር ሲሚንቶ ኢንተርፕራይዝ የነበራቸውን የቦርድ አባልነት እንዲሁም የደህንነት ሠራተኛነታቸውን መከታ በማድረግ፣ የአክሲዮን ማህበራቱ 310 መጽሐፍትን በ62ሺ ብር እንዲገዙ ካስደረጉ በኋላ፤ ገንዘቡንም መጽሐፍቱንም ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸው ተጠቅሷል፡፡ በመዝገቡ በ2ኛነት የቀረበውም ክስ ደግሞ ግለሰቡ የደህንነት ሠራተኛ መሆናቸው የፈጠረላቸውን ተሠሚነት እንደመልካም አጋጣሚ በመውሰድ፣ ወደ 26 የሚሆኑ ኩባንያዎችና ባለሀብቶች የተለያየ ብዛት ያላቸውን መጽሐፍት እንዲገዙ ካስደረጉ በኋላ፣ መጽሐፍቶቹን ሳያስረክቡ ለግል ጥቅማቸው አውለዋል ይላል፡፡ ከእነዚህ መካከል የአልሣም ኃላ.የተ.የግ ማህበር ባለቤት አቶ ሣቢር አረጋው፤ ያለፍላጐታቸው በሌላ መዝገብ ክስ በቀረበባቸው በአቶ ገብረዋህድ ወ/ጊዮርጊስ እና በባለሀብቱ በአቶ ነጋ ገ/እግዚአብሔር በኩል 500 መጽሐፍትን በመቶ ሺህ ብር እንዲገዙ ካስደረጉ በኋላ መጽሐፍቱን ለግላቸው አስቀርተው መጠቀማቸው፣ ጌታስ ትሬዲንግ 1500 መጽሐፍትን፣ ነፃ ፒኤልሲ 700፣ ካንትሪ ትሬዲንግ 300፣ ሐበሻ ካፒታል ሠርቪስ 50፣ አኪር ኮንስትራክሽን 100 መጽሐፍትን እንዲሁም በርካታ ድርጅቶችና ግለሰቦች የተለያየ ብዛት ያላቸውን መጽሐፍት እንዲገዙ ካደረጉ በኋላ፣ መጽሐፍቶቹን ሳያስረክቡ ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸው ተመልክቷል፡፡

በግለሰቡ ላይ በ3ኛነት በቀረበው ክስ፣ የተሰጣቸውን ሃላፊነት ያለአግባብ በመጠቀም በመዝገቡ ስሟ የተጠቀሰን ግለሰብ በመንግስት መኪና ቁልቢ ድረስ እንድትሄድና በተለያየ ጊዜ እንድትዝናና አስደርገዋል እንዲሁም ግለሰቧ ለነበረባት የፍትሃብሔር ክርክር የመ/ቤቱን ሠራተኛ መድበው፣ መደበኛ ስራውን ትቶ እንዲከታተል አስደርገዋል ይላል፡፡ በ4ኛ እና በ5ኛነት የቀረቡባቸው ክሶችም፤ ስልጣናቸውን መከታ በማድረግ፣ አቶ ሣቢር አርጋው የተባሉት ባለሃብት ጋ በመደወል፣ ለሚሠሩት ቤት ሴራሚክ እንደጐደላቸው በመንገር፣ ግለሰቡ በ65ሺህ ብር እንዲገዙላቸው ማስደረጋቸው እንዲሁም ከመጽሐፍቶቹ ሽያጭ መንግስት ይፈልገው የነበረውን ከ496ሺህ ብር በላይ ግብር አሳውቀው አለመክፈላቸው በአቃቤ ህግ የክስ ዝርዝር ላይ ቀርቧል፡፡ ቀሪዎቹ ክሶች ከቤተሰብ አባላቱ ጋር ተጣምረው የቀረቡ ሲሆን በመዝገቡ ከ6ኛ እስከ 9ኛ ክስ ሆኖ የቀረበው፣ አቶ ወልደስላሴ፤ 2ኛ ተከሣሽ የሆኑትን ወንድማቸው አቶ ዘርአይን የመኖሪያ ቤታቸው ወኪል በማድረግ፣ ቤቱ ከመኖሪያ ቤት ውጪ ለሆነ አገልግሎት እንዲውል ካደረጉ በኋላ፣ መንግስት ይፈልገው የነበረውን ከ126ሺ ብር በላይ ግብር በተገቢው መንገድ አሳውቀው አልከፈሉም፤ በዚህም የሃሰት ወይም አሳሳች መረጃ በማቅረብ ወንጀል ተከሰዋል ይላል፡፡ በተጨማሪም ከ119ሺ ብር በላይ የተርን ኦቨር ታክስ ግብርም አልከፈሉም ተብሏል፡፡

በሁሉም ላይ የቀረቡት ቀሪዎቹ ክሶች ምንጩ ያልታወቀ ሃብት ይዞ መገኘት የሚሉ ናቸው፡፡ 1ኛ ተከሣሽ ለወንድም እና እህቶቹ እንዲሁም ለቅርብ ጓደኛው ውክልና እየሰጡና ንብረትን በማስተላለፍ ዘዴ እየተጠቀሙ ሃብት አፍርተዋል ይላል፡፡ ምንጩ ያልታወቀ ሃብት ተብለው ከተጠቀሱት መካከልም በአቶ ወልደስላሴ እና በባለቤታቸው ስም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አምስት የተለያዩ ቅርንጫፎች ከ9ሺ እስከ 1 ሚሊዮን 5 መቶ ሺ ብር በማስቀመጥና በማንቀሳቀስ ሲጠቀሙ እንደነበር ተመልክቷል፡፡ ይህ ሲሆን የግለሰቡ ደሞዝ ከ1600 እስከ 6ሺህ ብር ነበር ብሏል አቃቤ ህግ፤ ሁለተኛ ተከሣሽ ደግሞ በመከላከያ ውስጥ ተቀጥሮ ሲሠራ ደሞዙ 523 ብር ሆኖ ሳለ፣ በ3 የንግድ ባንክ ቅርንጫፎች ከ150 ሺ እስከ 2 ሚሊዮን ብር ሲያንቀሳቀስ እንደነበር ተመልክቷል፡፡ ምንም የገቢ ምንጭ እንደሌላት የተገለፀው እህቱ እና ጓደኛውም በውክልና እና በማስተላለፍ ሂደቶች የእርሻ ልማት ኢንቨስትመንት እና በአዲስ አበባ፣ በመቀሌ እና በአክሱም ቦታ እና ቤት፣ እንዲሁም በባንክ የተለያየ መጠን ያለው ገንዘብ አስቀምጠው መገኘታቸው በአቃቤ ህግ የክስ ዝርዝር ተቀምጧል፡፡ በእለቱ ክሣቸውን ፍ/ቤቱ በንባብ ካሠማ በኋላ፣ 3ኛ እና 4ኛ ተከሣሽ ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ የአቃቤ ህግን መልስ መነሻ በማድረግ ውድቅ ካደረገ በኋላ፣ ተከሣሾች የሚያቀርቡትን መቃወሚያ ወይም መከራከሪያ ለመጠባበቅ መዝገቡን ለታህሣስ 7 ቀን 2006 ዓ.ም ቀጥሯል፡፡