Friday, October 31, 2014

የአፍሪካ ጸደይ"ኮምፓዎሬ “ደህና ሁኑ”!!!!!ቡርኪናፋሶን ያለገደብ ሲመሩ የነበሩት ብሌዝ ኮምፓዎሬ ለተጨማሪ ዓመታት ሥልጣናቸውን ለማራዘም ያደረጉት ሙከራ በመክሸፉ ከሥልጣናቸው እንደሚለቁ ገለጹ፤ ለአንድ ዓመት የመሸጋገሪያ መንግሥት ተመስርቶ ምርጫ እስከሚደረግ በሥልጣን እንደሚቀጥሉ አስታወቁ፡፡ ሕዝቡና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ግን ይህንን የሚቀበሉበት ትከሻ እንደሌላቸውና የኮምፓዎሬ አገዛዝ አሁኑኑ መውረድ እንዳለበት በተቃውሟቸው እየገለጹ ነው፡፡ ከ27ዓመት አምባገነናዊ ሥርዓት በኋላ ቡርኪናፋሶ ወደ ሌላ አምባገነናዊ ሥርዓት ልትሄድ እንደምትች ተጠቆመ፡፡

በቀድሞው ፕሬዚዳንት ቶማስ ሳንካራ ዘመን የመንግሥት ባለሥልጣንና የሳንካራ ወዳጅ የነበሩት ብሌዝ ኮምፓዎሬ፤ ቶማስ ሳንካራ ባልታወቀ ሁኔታ በመፈንቅለ መንግሥት ከተገደሉ ከዛሬ 27ዓመት ጀምሮ ቡርኪናፋሶን መግዛት ጀመሩ፡፡ መፈንቅለ መንግሥቱን በመምራት የተሳተፉት ኮምፓዎሬ የሳንካራን መገደል በወቅቱ “ድንገተኛ” በማለት ከመጥቀስ በስተቀር ምርመራ እንዲካሄድ አላዘዙም፤ ምስጢሩም እንዳይወጣ ተደርጎ ቆይቷል፡፡

ቶማስ ሳንካራን ከሥልጣን ካስወገዱ በኋላ ለሦስት ዓስርተ ዓመታት ያህል የዘለቀውን አገዛዛቸውን የጀመሩት ኮምፓዎሬ እኤአ በ1990ዎቹ በተደጋጋሚ የተመረጡት ሲሆን የአገሪቱ ሕገመንግሥት ከተሻሻለ በኋላ በሁለት ሺዎቹም ሁለት ጊዜ ተመርጠዋል፡፡

በአገዛዝ በቆዩበት ዘመን ሁሉ የአውሮጳውያንና የአሜሪካ ወዳጅ በመሆን ሥልጣናቸው ሳይደፈር በአምባገነንነት ለመቆየት ችለዋል፡፡ አክራሪ እስላማዊነትን እዋጋለሁ በማለት የአሜሪካ ወዳጅነታቸውን ያጠናከሩት ኮምፓዎሬ በላይቤሪያና ሴራሊዮን እጅግ አስከፊ ጭፍጨፋ ያካሄዱትን እና በአሁኑ ወቅት 50ዓመት እስራት የተበየነባቸው የቀድሞው የላይቤሪያ መሪ ቻርልስ ቴለር የቅርብ ወዳጅ ነበሩ፡፡ ሳንካራን ለመገልበጥና ለመግደል የቴይለር ጦር እንደተሳተፈና በምላሹ ኮምፓዎሬ ለቴይለር ወደ ሥልጣን መምጣትና ከዚያ ጋር ተያይዞ ለተፈጸመው ወንጀል ተባባሪ ናቸው በማለት ሁኔታዎችን የሚያገናኙ ወገኖች አሉ፡፡

በአገራቸው የሚነሱ ተቃውሞዎችን ስልታዊ በሆነ መንገድና በምዕራባውያን ድጋፍ ሲያከሽፉ የኖሩት ብሌዝ ኮምፓዎሬ በአካባቢው አገራት ዘንድ የሰላም ዘንባባ አቅራቢ፣ አስታራቂ፣ አስማሚ፣ ሸምጋይ፣ … ሆነው ምስላቸውን እና ማንነታቸውን ሲገነቡ ቆይተዋል፡፡ በአምባገነንነት በቆዩባቸው ዓመታት በሙስና በተለይም ከአልማዝ ሽያጭ ከሚገኘው ገንዘብ ያላቸው ተሳታፊነት ከፍተኛ እንደሆነ ይነገራል፡፡

በቀጣዩ የአውሮጳውያን ዓመት 2015 ሥልጣናቸው የሚያበቃው ኮምፓዎሬ “ደህና ሁኑ” ብለው ለመሄድ የተዘጋጁ አልነበሩም፡፡ በመሆኑም የአገሪቱን ሕገመንግሥት በማሻሻል እንደገና ለመመረጥ ደፋ ቀና ማለት ጀመሩ፡፤ ፓርላማቸውን አሰብስበው ሕገመንግሥቱ እንዲሻሻል በማድረግ ሂደት ላይ እያሉ ሕዝቡ “በቃኝ” አለ፡፡

የ27 ዓመታት አገዛዝ የመረራቸው ዜጎች ሐሙስ ዕለት ፓርላማውን ጥሰው በመግባት ድምጽ እንዳይሰጥ ከማድረግ አልፈው በእሣት አጋዩት፡፡ ተቃውሞ በየቦታው ፈነዳ፡፡ ቡርኪናፋሶ መጋየት ጀመረች፡፡ ሁኔታው ያላማራቸው ኮምፓዎሬ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጁ፡፤ ሰሚ ግን አላገኙም፡፡ ሕዝቡ “ይህንን አገዛዝ አንፈልግም፣ በቃን” አለ፡፡ ሕዝባዊ ዓመጽ በየቦታው ተቀጣጠለ፡፡ በተለይ ዋና ከተማዋ ዖጋዱጉ የዓመጹ ዋና ማዕከል ሆነች፡፡

መንግሥት ሥራ አቆመ፣ ፓርላማውም ፈረሰ፡፡ ድህነት ያስመረራቸው ዜጎች አሁንም ተቃውሟቸውን ቀጥሉ፡፡ ኮምፓዎሬን ማየትም ሆነ መስማት በጭራሽ አይፈልጉም፡፡ ወታደሮች በየአካባቢው ሥነሥርዓት ለማስጠበቅ እየጣሩ ቢሆንም ዓመጹ ግን ቀጥሏል፡፡ ንብረት እየወደመ ነው፤ ባንኮችም ተዘርፈዋል፡፡

ዛሬ አርብ ዳግም ለመመረጥ ሲመኙ የነበሩት ኮምፓዎሬ ሥልጣን በቃኝ፤ መንግሥት ፈርሷል፤ ፓርላማውም አይሰራም፤ ከሥልጣኔ እለቃለሁ ነገር ግን በ2015 ምርጫ እስከሚካሄድ የሽግግር አስተዳደር ተመስርቶ ሁሉም ነገር መረጋጋት አለበት በማለት አስቀድሞ በተቀዳ የቴሌቪዥን መልዕክት ቢያስተላልፉም ሰቆቃ የመረራቸው፣ ኑሮ ያቃጠላቸው፣ ነጻነት የጠማቸው ዜጎች ግን አሁንም “አንሰማም” ብለው ተቃውሟቸውን በመቀጠል ፕሬዚዳንቱ ከሥልጣን እንዲወርዱ ጠይቀዋል፡፡

ሰላሳ አራት የሚሆኑ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ፕሬዚዳንቱ ያቀረቡትን ቅደመ ሁኔታ አንቀበልም ብለዋል፡፡ ለኮምፓዎሬ ምላሽ ሲሰጡም “አንድ የምንቀበለው አጭርና ግልጽ ቅድመ ሁኔታ ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ብሌዝ ኮምፓዎሬ ከሥልጣን እንዲለቁ ነው” በማለት ተናግረዋል፡፡

ጦሩ ሥልጣኑን የተረከበ እንደሆነ እየተጠቆመ ሲሆን አገሪቱን በበቂ ሁኔታ ለማረጋጋት እንዳልቻለ ከዋና ከተማዋ የሚመጡ ዜናዎች ይጠቁማሉ፡፡ የሕዝቡ ዓመጽም ወደ ሌሎች ከተሞች እየተዛመተ መሆኑን ከተለያዩ የዜና ማሰራጫዎች እየተሰማ ነው፡፡

በአንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ዘንድ ከአረብ ጸደይ ቀጥሎ የተጀመረ “የአፍሪካ ጸደይ” ሊሆን ይችላል በማለት ግምት የሰጡበት የቡርኪናፋሶ ሕዝባዊ አመጽ ተመልሶ በአምባገነናዊ አገዛዝ እንዳይወድቅ ስጋት አላቸው፡፡ ለዚህም ጠንካራ ተቋማት መመሥረት አስፈላጊነትን ያሰምሩበታል፡፡ በተለይ ከአምባገነናዊ አገዛዝ ወደ ሕዝባዊ ሥርዓት በሚደረግ ጉዞ በቅድሚያ የሚደረጉ መሰናዶዎች ሳይከናወኑ በጭፍን አምባገነኖችን ከሥልጣን እንዲወርዱ ማድረግ በበርካታ አገራት እንደተደረገው መልኩን የቀየረ አምባገነናዊ ሥርዓት ለመመሥረት እንደሚጋብዝ ይናገራሉ፡፡ ከዚህ አንጻር የሕዝብ ንቃተ ኅሊና መዳበር፣ የእርሰበርስ ውይይት መጀመር፣ የተቋማት መመሥረት፣ … ወሳኝነት ያላቸው ቅድመ ሁኔታዎች እንደሆኑ ያሰምሩበታል፡፡

ይህንን ዘገባ ካጠናቀርን በኋላ ከቢቢሲ የተገኘው ዜና እንደሚያመለክተው ከሆነ ፕሬዚዳንቱ ሥልጣናቸውን ጥለው ከአገር እየወጡ እንደሆነ የጦሩ ጄኔራል ዖኖሬ ትራዖሬ በሕገመንግሥቱ መሰረት አገሪቷን እየመሩ እንደሆኑ አስታውቀዋል፡፡ የፕሬዚዳንቱ ቦታ ባዶ እንደሆነና በ90 ቀናት ውስጥ ምርጫ እንዲካሄድ መነገሩን ቢቢሲ ጨምሮ ዘግቧል፡፡ ብሌዝ ኮምፓዎሬ አሁን ያሉበት ቦታ ባይታወቅም በአቅራቢያ ባለ አገር አቋርጠው ወደ አንድ አውሮፓ ምናልባትም ፈረንሳይ የስደት ህይወታቸውን መምራት ይጀምራሉ የሚል ግምት እንዳለ እየተነገረ ነው፡፡

Wednesday, October 29, 2014

Ethiopian court sentences journalist to three years in prison

Nairobi, October 27, 2014--The Committee to Protect Journalists condemns today's sentencing of Ethiopian journalist Temesghen Desalegn to three years' imprisonment on charges of defamation and incitement that date back to 2012. A court in Addis Ababa, the capital, convicted Temesgen on October 13 in connection with opinion pieces published in the now-defunct Feteh news magazine, according to news reports. He was arrested the same day. Authorities have routinely targeted Temesghen for his writing. Temesghen's lawyer said he plans to appeal the ruling, according to local journalists.


https://cpj.org/2014/10/ethiopian-court-sentences-journalist-to-three-year.php

Saturday, October 11, 2014

እስር ቤት ውስጥ የሚገኙት ኢትዮጵያውያን መልዕክት!!!

  አቶ በቀለ ገርባን፣ አቶ ኦልባና ሌሊሳን፣ አዛውንቱን ሲሳይ ብርሌን፣ አቶ ጉታ ዋቆንና ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬን አግኝተዋል፡፡ 
‹‹ህብረ ብሄር ፓርቲዎች ተጠናክረው የብሄር ፓርቲዎችን ማጥፋት አለባቸው›› አቶ በቀለ ገርባ
ከዝዋይ ወደ ቃሊቲ ከመጣሁ 11 ወራት ሆኖኛል፡፡ በህዳር ወር 2006 ዓ.ም ነው ወደ ቃሊቲ የመጣሁት፡፡ በአሞክሮዬ መሰረት ጥር 11 ቀን 2006 ዓ.ም መፈታት ቢገባኝም አሁንም ድረስ እስር ቤት ውስጥ እገኛለሁ፡፡ በወቅቱ በአሞክሮዬ መሰረት መፈታት እንዳለብኝ ለእስር ቤቱ ኃላፊዎች ደብዳቤ ጽፌ ነበር፡፡ ሊፉቱ ሲፈልጉ አስጠርተው ያነጋግሩሃል፡፡ ካልፈለጉ ደግሞ ዝም ይሉሃል፡፡ እኔ ደብዳቤ ብጽፍም አልተጠራሁም፡፡ ምክንያታቸውን ባላውቅም ሊፈቱኝ አልፈለጉም ማለት ነው፡፡ ግን በአሞክሮዬ ባለመፈታቴ አልተጎዳሁም፡፡ በርካታ ነገሮችን ተምሬበታለሁ፡፡ እንዲያውም የሚጎዱት እነሱው ራሳቸው ናቸው፡፡ በርካታ ታሳሪዎች አሳሪዎቹ ለቃላቸውም ሆነ በህጉ ተገዥ እንዳልሆኑ በእኔ ጉዳይ ተምረዋል፡፡ አሁን በመጋቢት ወር ዋናውን ፍርድ ጨርሼ እፈታለሁ ብዬ እጠብቃለሁ፡፡
እኔ የማምነው በባለሙያነቴ ነው፡፡ ፖለቲከኛ ነኝ ብዬ አላምንም፡፡ እንደዛም ሆኖ ግን እንደ ግለሰብ ፍትህን እሻለሁ፡፡ ስልጣን ላይ ማንም ይምጣ ማን ፍትህን የሚሰጥ ከሆነ ችግር የለብኝም፡፡ በሙያተኝነቴ ነው መቀጠል የምፈልገው፡፡ ነገር ግን ክፍቶች አሉ፡፡ ወደ ፖለቲካው የገባሁትም ክፍተቶችን በማየቴ ነው፡፡
ህብረ ብሄራዊ የሚባሉ ፓርቲዎች ለአብዛኛው ህዝብ ተደራሽ አይደሉም፡፡ የህብረ ብሄር ፓርቲዎች ድክመት ደግሞ የብሄር ፓርቲዎች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል፡፡ በእነሱ መዳከም ነው የብሄር ፓርቲዎች በየ ቦታው ለመመስረት እድል የሚያገኙት፡፡ ህብረ ብሄር ፓርቲዎች የአንድን ማህበረሰብ ችግር ለመፍታት አቅም የላቸውም ብሎ ያሰበ አካል/ሰው እወክለዋለሁ በሚለው ማህበረሰብ ስም ፓርቲ ያቋቁማል፡፡ እኔም በዚህ ክፍተት ነው ወደ ፖለቲካው የገባሁት፡፡ ይህ ችግር ባይኖር ማህበረሰብን ከፋፍሎ ‹‹ይህኛው ፓርቲ የዚህ፣ ያንኛው ደግሞ የዚህኛው ማህበረሰብ ፓርቲ ነው›› ተብሎ እንዲከፋፈል ፍላጎት የለኝም፡፡
ህብረ ብሄራዊ ፓርቲዎች ቢጠናከሩ በአንድነት መታገልን የመሰለ ነገር የለም፡፡ ከአንዱ ዓለም አራጌ ጋር በታሰርንበት ወቅት ‹‹እናንተ ከተጠናከራችሁ እኛ እንጠፋለን፡፡ እናንተ ተጠናክራችሁ በብሄር የተደራጀነውን ማጥፋት አለባችሁ፡፡ ተጠናከሩና እኛን አጥፉን፡፡ ያኔ ሁላችንም በአንድነት እንታገላለን፡፡ ችግሮችም ይፈታሉ›› እለው ነበር፡፡ የህብረ ብሄራዊ ፓርቲዎች አለመጠናከር እንጅ ለዚህኛው አሊያም ለዛኛው ህዝብ ብዬ መስራት አልፈልግም፡፡ በአንድነት መስራትን የመሰለ ነገር የለም፡፡
ህብረ ብሄር ፓርቲዎች በአንድ በኩል በመረጃ እጥረት፣ በሌላ በኩል በስህተት፣ አሊያም አይቶ በማለፍ የአንድን ማህበረሰብ ችግር ችላ ይሉታል፡፡ ይህ ነው ተነጣጥሎ ለመታገል፣ ለብሄር ፓርቲዎች መበራከት ምክንያት የሆነው፡፡ ህዝብ መብቱ እስከተከበረለት ድረስ ማን መጣ ማን ትኩረት አይሰጥም፡፡ ህብረ ብሄር ፓርቲዎች መዳከም ግን የብሄር ፓርቲዎች ተደማጭነት እንዲያገኙ ምክንያት ሆኗል፡፡ አሜሪካን ለምሳሌ ብንወስድ ህዝቡ መብቱ እስከተከበረለት ድረስ ጥቁር መራ ነጭ ችግር የለበትም፡፡ የእኛ አገርም ጉዳይ ተመሳሳይ መሆን ይችላል፡፡ በዚህ ላይ እኛ ወንድማማቾች ነኝ፡፡
እኔ ህብረ ብሄር ፓርቲዎችን እወቅሳለሁ፡፡ እነሱ ከተጠናከሩ በየቦታው በተናጠል የሚደረገው ትግል ወደ አንድ ጠንካራ ትግል ይመጣል፡፡ እነሱ ከተጠናከሩ በተናጠል የሚደረገው ጭቆና ይቀንሳል፡፡ ክፍተት ባይኖርና ህብረ ብሄር ፓርቲዎች ለሁሉም ህዝብ መድረስ ቢችሉ እኔ በሙያዬ በቀጠልኩ ነበር፡፡ እንዲህ የምንታሰረውም እኩ ከድክመታችን የተነሳ ነው፡፡ ጠንካራ ህብረ ብሄራዊ ፓርቲ ቢኖረን እኮ እኛም አንተሰርም ነበር፡፡ ይህ ካልሆነ ግን የአገራችንን ችግር መፍታት አንችልም፡፡ በተናጠል ለጭቆና እንዳረጋለን፡፡ በተናጠል እንታሰራለን፡፡ በሂደት ጭቆናውን እየለመድነው እንሄዳለን፡፡ በዚህ ሁኔታ ለውጥ ማምጣት አንችልም፡፡
‹‹ኢትዮጵያ ጭንቅ ላይ እንዳለች እርጉዝ ሴት ነች›› አቶ ሲሳይ ብርሌ
የተፈረደብኝ 13 አመት ነው፡፡ ከታሰርኩ አራት አመት ሆኖኗል፡፡ እድሜየ 65 ደርሷል፡፡ እስር ቤት ውስጥ ችግር አለ፡፡ የእስር ቤቱን ኃላፊዎች የምናገኛቸው ህክምና ስንፈልግ ነው፡፡ ነገር ግን የህክምናው ጉዳይ ባይወራ ይሻላል፡፡ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ በእርግጥ ውጭ ያለው ህዝብም በሰፊው እስር ቤት ውስጥ እንዳለ ነው የሚቆጠረው፡፡ ልዩነቱ የተሻለ ነፋስ ስለምታገኙ፣ ስለምትዘዋወሩና የፈለጋችሁትን ሰውም ስለምታገኙ ነው፡፡
እኛ እያረጀን ነው፡፡ ከእድሜያችን አንጻር በትግሉ ሂደት ብዙም የምንጨምረው ነገር ላይኖር ይችላል፡፡ እናንተ ወጣቶች ናችሁ፡፡ ለትግሉ መሰረት የምትጥሉበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ ወጣትነት ለትግል ወሳኝ ጊዜ ነው፡፡ አባት ያላወረሰውን ልጅ ሊያስቀጥል አይችልም፡፡ እናንተ አሁን ለራሳችሁ ብቻ ሳይሆን ለልጆቻችሁም ጭምር ነው የምትታገሉት፡፡ እናንተ በርትታችሁ ካልታገላችሁ ልጆቻችሁ ምንም የሚወርሱት ነገር አይኖርም፡፡ አባት ያላወረሰውን ደግሞ ልጅ ምንም ነገር ሊያስቀጥል አይችልም፡፡ በመሆኑም እናንተ ከአሁኑ ለእውነት በመቆም ልጆቻችሁ የሚያስቀጥሉት ነገር መስራት አለባችሁ፡፡
ጭቆና እስካለ ድረስ እኔም ሆንኩ እናንተ ባንታገልም ጭቆናውን ለማስወገድ የሚነሳ ሰው አይጠፋም፡፡ እናንተን እድለኛ የሚያደርጋችሁ ጭቆናውን ለመግታት ፈልጋችሁ፣ በራሳችሁ ተነሳሸነት በመጀመራችሁ ነው፡፡
ጭንቅ ላይ ያለች እርጉዝ ሴት ካላማጠች አትገላገልም፡፡ ለእኔ ኢትዮጵያ ጭንቅ ላይ እንዳለች እርጉዝ ሴት ነች፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ከሚደርስባት ስቃይ ለመገላገል ማማጥ አለባት፡፡ ያኔ ትገላገለዋለች፡፡ ለዚህ ደግሞ ትግል ያስፈልጋል፡፡ ወጣቶች መታገል አለባችሁ፡፡ ትግሉ ጥንካሬን ይጠይቃል፡፡ መጠንከር አለባችሁ፡፡
‹‹ተቃዋሚዎች በምርጫው ካላመኑበት ሁላችንም አንገባም ማለት አለባቸው›› አቶ ኦልባና ሌሊሳ
የፖለቲካ ፓርቲዎች ስለ ምርጫው ቀድመው መስራት አለባቸው፡፡ ምርጫ ስለመግባት አለመግባት ከመወሰናቸው በፊት ጠንክረው መስራት ይገባቸዋል፡፡ ውሳኔውን ከመወሰናቸው በፊት ውሳኔውን ተከትሎ ሊመጣ የሚችለውን ነገር ማሰብ አለባቸው፡፡ ይህ ጉዳይ ጥናት ያስፈልገዋል፡፡ ለውሳኔያቸው ደግሞ ተገዥዎች መሆን አለባቸው፡፡ አንዴ ከተወሰነ በኋላ ጠንካራ አቋም መያዝ አለበት፡፡ በህዝቡ አመኔታ ለማግኘት በውሳኔያቸው መጽናት አለባቸው፡፡ መወላወል አይገባም፡፡ ጊዜው እስኪደርስ ጠንክረው መስራት አለባቸው፡፡ በአንድ ወቅት 33 የሚባል ስብስብ ነበር፡፡ አሁንም ተባብሮ መስራት ያስፈልጋል፡፡ ለምርጫው በጋራ መስራት ያስፈልጋል፡፡
ተቃዋሚዎች በምርጫው መሳተፍ ለህዝብ የማይጠቅም መሆኑን ካመኑ እና መግባት የማያስፈልጋቸው ከሆነ በአንድነት ኃይልን አሰባስቦ ከምርጫው መውጣት ይቻላል፡፡ በምርጫው ካላመኑበት ሁላችንም አንገባም ነው ማለት ያለባቸው፡፡ በተናጠል ከምርጫው ራስን ማግለል ጥቅም አይኖረውም፡፡ በእርግጥ ይህ መወሰን ያለበት ጊዜው ሲደርስ ነው፡፡ እስከዛ ግን ጠንክረው መስራት አለባቸው፡፡
መጥታችሁ ስለጠየቃችሁን በጣም እናመሰግናለን፡፡ ውጭ ያለውን የቤት ስራችሁንም ጠንክራችሁ መስራት አለባችሁ፡፡
ነገረ ኢትዮጵያ በቀጣይ ጊዜያትም እስር ቤት ውስጥ የሚገኙትን ሌሎች ኢትዮጵያውያን መልዕክት ለማቅረብ ትጥራለች፡፡