Friday, February 6, 2015

የዞን ዘጠኝ ተከሣሾች የመሃል ዳኛው እንዲቀየሩ ጠየቁ!

የዞን ዘጠኝ ጋዜጠኞችና የኢንተርኔት ፀሐፊዎች

እሥር ቤት ውስጥ የሚገኙት ዘጠኝ ጋዜጠኞችና የኢንተርኔት ፀሐፍት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ሰብሳቢ ዳኛ ከዚህ በኋላ ጉዳያቸውን እንዳይመለከቱ ያቀረቡት አቤቱታ ውድቅ ተደርጓል፡፡
አቤቱታ ያቀረቡባቸው ዳኛ ግን በራሣቸው ፈቃድ ጉዳዩን ላለማየት መወሰናቸውን ገልፀዋል።
 
ፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ
የዞን ዘጠኝ ጦማርያንና ጋዜጠኞችን ጉዳይ የሚመለከተው የልደታው ችሎት ለተከታታይ ሁለት ቀናት የሚሰጠው ውሳኔ ምን ሊሆን እንደሚችል በጉጉት ሲጠበቅ ነበር። በተለይም ጦማርያኑ እና ጋዜጠኞቹ የመሃል ዳኛው ስራቸውን በሚገባ እያከናወኑ ስላልሆነ፤ እንዲነሱላቸው ነበር በደብዳቤ የጠየቁትከተከሳሾቹ አንዱ አቤል ዋበላ እሥር ቤት ውስጥ ግፍ እንደተፈፀመበት ለፍርድ ቤቱ አቤት ብሎ መፍትሔ እንዲሰጠው አመልክቷል፡አቤል ዋበላ እንደትላንት ከፍርድ ቤቱ ወደ ቅሊንጦ ማረሚያ ቤት ሲወሰድ፤ ፖሊሶቹ እረስተው በእጁ ካቴና ሳያስገቡ ቀርተው ነበር። ያለካቴና ቅሊንጦ ከደረሰ በኋላ ግን የደረሰበትን ስቃይ ሲያስረዳ በፍርድ ቤቱ ውስጥ የተገኙት በሙሉ አዝነው ነበር። “ቅሊንጦ ስንደርስ እጄ ላይ ካቴና ስላልነበረ፤ የማረሚያ ቤቱ ሰራተኞች እየሰደቡ እና እያንገላቱ እጄን በውሻ ሰንሰለት አስረው ነው ያሳደሩኝ” በማለት እንባ እየተናነቀው ነበር የተናገረው። “ሌላው ቀርቶ ማዕከላዊ እያለሁ በደረሰብኝ ከፍተኛ ድብደባ ምክንያት አንድ ጆሮዬ በደንብ አይሰማም። በመሆኑም ለመስሚያ የሚያገለግለኝን የጆሮ ማዳመጫዬንም ወስደውብኛል” በማለት የደረሰበትን ግፍ እና በደል አስረድቷል።
ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ለማየት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡