Wednesday, February 19, 2014

የካቲት 12

በኢጣሊያ መንግሥት የኢትዮጵያ ወኪል አገረ ገዢ የነበረው ማርሻል ሩዶልፎ ግራዚያኒ፣የኔፕልስ ልዕልት ልጅ መውለዷን ምክንያት በማድረግ በቤተመንግሥቱ ለድሆች ምጽዋት ለመስጠት ስለፈለገ የከተማው ድሆች እንዲሰበሰቡ አዝዞ፣ ሶስት ሺህ የሚሆኑ ምንዱባኖች በቅጥሩ ውሥጥ ተኮልኩለው ነበር፡፡ ለእያንዳንዱ ደሀም ሁለት የማርትሬዛ ብር እንዲሰጥ ተወስኖ ነበር፡፡

በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ ራሱ ጀነራል ግራዚያኒ፣ የሜትሮፖሊታን ጳጳስ አቡነ ኪርል እንዲሁም ታላላቅ የኢጣሊያ ሹማምንት ተገኝተው ነበር፡፡

እኩለ ቀን ሲሆን ግራዚያኒ በቤተ መንግሥቱ መግቢያ ደረጃ ላይ ሆኖ ለተሰበሰበው ሕዝብ ዲስኩር ማሰማት እንደጀመረ በግቢው በር በኩል ሁለት ቦምቦች ተከታትለው ፈነዱ፡፡ ለሶስተኛ ጊዜ የፈነዳው ቦምብ ግን ከፍተኛ የፋሺስት ኢጣሊያ ባለሥልጣናት ከተቀመጡበት መካከል አረፈ፡፡ በቀጣዮቹ ደቂቃዎች አራት ተጨማሪ ቦምቦች ተወርውረው ፈነዱ፡፡ማርሻል ግራዚያኒ ጀርባውን ቆስሎ ወደቀ፣ የኢጣሊያ አየር ኃይል አዛዥ የነበረው ጀነራል አውሬሊዮ ሊዮታ ቀኝ እግሩንና ቀኝ ዐይኑን አጣ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጉይዶ ኮርቲሲ እና ሌሎች ኢጣሊያውያን እንግዶች በፈንጂው ተጎዱ፡፡ ፍንዳታው ጋብ ሲል ከንቲባ ኮርቴሲ ከወደቀበት ተነስቶ የተሰበሰቡት ኢትዮጵያውያን ላይ በማነጣጠር የመጀመሪያውን ጥይት ተኮሰ፤ የፋሺስት ፖሊሶችም ምሣሌውን በመከተል ሶስት ቀን የሚቆየውንና መላውን ከተማውን ያዳረሰውን አሰቃቂ ጭፍጨፋ ከዚያው ከቤተ መንግሥት ውሥጥ ጀመሩ፡፡
በደረሰበት የፈንጂ አደጋ ማርሻል ግራዚያኒ በ350 ፍንጣሪዎች ቆስሏል፡፡

የካቲት 12 ቀን ስለ ደረሰበት አደጋ ግራዚያኒ ለኢጣሊያ ቅኝ ግዛቶች ሚኒስትር ባስተላለፈው ቴሌግራም ‹‹ ዛሬ ጠዋት በ5 ሠዓት ግቢ ተገኝቼ ነበር፡፡
ታላላቅ መኳንንት፣ የኦርቶዶክስና የእስልምና ሀይማኖት መሪዎች ሁሉ ተሰብስበው ነበር . . . 6 ሠዓት ሲሆን አሥር የብሬዳ የእጅ ቦምቦች ካልታወቁ ሠዎች ተጣሉብን፡፡
በዚህም ምክንያት ሠላሳ ሰዎች ቆሰሉ፡፡ በኔ መቁሰል ምክንያት አገሪቱን የተከበሩ ፔትሬቴ እና ጀነራል ጋሪባልዲ እንዲጠብቁ አድርጌአለሁ፡፡ ለአዲስ አበባ ከተማ ጸጥታም አላፊ አድርጌያቸዋለሁ›› ብሏል፡፡ ግራዚያኒ በሌላ ጊዜ ወደ ሮማ ባስተላለፈው ቴሌግራሙ የተደረገበትን የመግደል ሙከራ አስመልክቶ ሲጽፍ ‹‹የተጣለብኝ ቦምብ ቢያንስ 18 ይሆናል፡፡

አሳባቸው ባንድ ፈንጂ እኔን ብቻ ሳይሆን ሌሎቹንም የመንግሥቱ ባለሥልጣኖች ጠራርጎ ለማጥፋት ነበር . . .
በተጣለብኝም ቦምብ 250 ፍንጥርጣሪ ብረቶች ከገላዬ ወጥተዋል፡፡ እነዚህንም ፍንጣሪዎች ለታላቅ መታሰቢያነት አስቀምጫቸዋለሁ›› ብሏል፡፡

ለዚህ በግራዚያኒ እና በሌሎች የፋሺስት ኢጣሊያ ባለሥልጣኖች ላይ ለተጣለ አደጋ የኢጣሊያ ፖሊሶች (ካራቢኔሪ)፣ ባለ ጥቁር ሸሚዞችና ወታደሩ የሰጡት ምላሽ ከማጥቃት ወሰን፣ ከውጊያ ደንብ እና ከጭካኔ ገደብ ያለፈ አሰቃቂ የጅምላ ጭፍጨፋ ነበር፡፡ በጊዜው አዲስ አበባ ውሥጥ ይሠራ የነበረ ዶክተር ላዲስላስ ሳቫ የተሰኘ ሀንጋሪያዊ ሐኪም የተመለከተውን የፋሺስቶች የግፍ ሥራ እንዲህ አስታውሶ ነበር:-
‹‹ምን ዓይነት አጨካከን ነው? ደም እንደ ውሃ ሲፈስ በየመንገዱ ላይ ያየሁት የዚያን ጊዜ ነው፡፡ የወንዶች፣ የሴቶችና የልጆች ሬሳ በያለበት ተኝቷል፡፡ ወዲያው ከባድ የቃጠሎ ጭስ ተነስቶ ከተማዋን አጨለማት፡፡ የሕዝቡ ቤት ከተፈተሸ በኋላ ሰዎቹ በውስጡ እንዳሉ ቤቱ በእሣት ይቃጠላል፡፡ ቃጠሎው ቶሎ እንዲያያዝም በቤንዚንና በዘይት ይጠቀሙ ነበር፡፡
ሰዉ እሣቱን እየሸሸ ከቤቱ ሲወጣ በመትረየስ ይገድሉታል . . . መኪናዎች እየዞሩ ሬሣ ያነሳሉ፡፡ ባለ ጥቁር ሸሚዞች ወደ ኢጣሊያ ባንክ እየገቡ ሌሊት የሠረቁትን ብርና ወርቅ ያስቀምጣሉ፡፡ ዘረፋው በቤት ውሥጥ ብቻ አልነበረም፡፡ ከሚገድሏቸው ሴቶች አንገትና ጆሮ ላይ የሚገኘውን ወርቅ ሁሉ ይወስዱ ነበር . . . ሕክምና በምሠራበት ቦታ ብዙ ኢጣሊያኖች ይመጡ ነበር፡፡ እያንዳንዱ ኢጣሊያዊ ምን ያህል ሰው እንደገደለ በኩራት ይናገራል፡፡ አንዳንዶች 80 ገደልኩ ሲሉ ሌሎች 100 እንደገደሉ ይናገራሉ፡፡ አንድ ኢጣሊያዊ ብቻ እያዘነ እኔስ የገደልኩት ሁለት ሰው ብቻ ነው ሲል ሰምቼዋለሁ፡፡ . . . የማልረሳው ነገር፤ ግድያው እንዲቆም በተደረገበት ጊዜ ታላቁ ግራዚያኒ ለሕዝብ በማዘን ግድያው ይቁም ብለዋል ተብሎ የተነገረው ነው፡፡ ግሩም አዘኔታ!››

ዐርብ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም ቀትር ላይ በግራዚያኒ ላይ ቦምብ የወረወሩት አብርሃ ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም የተባሉ ኤርትራውያን ወጣቶች ናቸው፡፡ የዚህ አደጋ ቀያሽ ሆኖ የሚቆጠረው አብርሃ ደቦጭ እና ጓደኛው ሞገስ አስገዶም የኢጣሊያ ወረራ ሲጀመር አዲስ አበባ በሚገኘው የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተማሪዎች ነበሩ፡፡ አብርሐ ደቦጭ ቀደም ብሎ የኢጣሊያ ቋንቋ ተምሮ ስለ ነበር ከወረራው በኋላ አዲስ አበባ ባለው የፋሺስት ፖለቲካ ቢሮ ተቀጥሮ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ አብርሃ ደቦጭ ይህ ስራው የፋሺስቶችን የግፍ አገዛዝና የዘር መድልዎ አሠራር በቅርብ ለማወቅ ስላስቻለው ጉዳዩን ከሞገስ አስገዶም እና ስብሐት ከተባለ በጀርመን ቆንስላ ከሚሰራ ጓደኛው ጋር ይወያይበት ነበር፡፡
ይህ ሁኔታም በፋሺስቶች ላይ እንዴት አደጋ መጣል እንዳለባቸው እንዲያውጠነጥኑ አድርጓቸዋል፡፡ አብርሐ ደቦጭ ወደፊት ላቀደው ጸረ ፋሺስት ጥቃት እንዲረዳው በባዶ እግሩ ከአዲስ አበባ 10 እና 15 ኪሎሜትሮች እየወጣ በጫካ ውስጥ ፈንጂ ለመወርወር የሚያስፈልገውን ልምምድ ያከናውን ነበር፡፡

አብርሐ ደቦጭ የቤት ዕቃዎቹን ሸጦ ባለቤቱን ደግሞ ወደ ደብረ ሊባኖስ ወስዶ በማስቀመጡ በፋሺስቶች ላይ አደጋ የሚጥልበትን ቀን አስቀድሞ የሚያውቀው ይመስላል፡፡ አብርሐ ደቦጭ በዚህ ዝግጅት ላይ እያለ ግራዚያኒ በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ድሆችን በመጥራት ምጽዋት ለመስጠት መወሰኑ ተሰማ፡፡ የካቲት 12 ቀን አብርሐ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም ከእንቅልፋቸው የነቁት ማልደው ሲሆን፣ የፋሺስት ኢጣሊያን ባንዲራ የሚኖሩበት ቤት ወለል ላይ በጦር ሰፍተውና የእጅ ቦምቦቻቸውን አዘጋጅተው ወደ ገነተ ልዑል ቤተመንግሥት አመሩ፡፡ በሥፍራው እንደደረሱም ወደ ዒላማቸው በድንጋይ ውርወራ ርቀት ያህል ቀረብ ካሉ በኋላ አመቺ ጊዜ ይጠባበቁ ጀመር፡፡ ስድስት ሰዓት ሆኖ ማርሻል ግራዚያኒ ንግግር ማድረግ ሲጀምር አከታትለው የእጅ ቦምቦችን ወረወሩበት፡፡ ፍንዳታው ያስከተለው ረብሻ ከመረጋጋቱና ፋሺስቶችም የመልሶ ማጥቃት እርምጃ ከመውሰዳቸው በፊት፣ አብርሀ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም በቤተ መንግሥቱ የጓሮ በር ሹልክ ብለው ለመውጣት ችለዋል፡፡
ፋሺስት ኢጣሊያ በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት የተጣለውን አደጋ ተዋናዮች አብርሐ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም መሆናቸውን ተረድቶ ስለነበር ‹‹አማጽያኑን›› ለሚይዝ ማንኛውም ሰው የ10 ሺህ ሊሬ ሽልማት እንደሚሰጥ አውጆ ነበር፡፡ አብርሃምና ሞገስ ግን መላውን የአዲስ አበባ ነዋሪ ያብረከረከው ጅምላ ጭፍጨፋ ሳይነካቸው ከመናገሻ ከተማው በሰላም ወጥተው ደብረ ሊባኖስ ለመድረስ ችለው ነበር፡፡ በዚያ ከደረሱ በኋላ በራስ አበበ አረጋይ ከሚመሩት የሸዋ አርበኞች ጋር መቀላቀላቸው ተረጋግጧል፡፡ ይሁን እንጂ ኤርትራውያኑ ወጣቶች ከኢጣሊያኖች ጋር ይሠሩ ስለነበረ የሸዋ አርበኞቹ እምነት ስላልጣሉባቸው ወደ ሱዳን ለመሄድ ፈቃድ ጠይቀው እንደተሰናበቱ ታውቆ ነበር፡፡

ሁለቱ ወጣቶቹ በጎጃም በኩል አድርገው ወደ ሱዳን ለመግባት ጥቂት ሲቀራቸው በድንበር አካባቢ ባልታወቁ ሰዎች መገደላቸው ተሰማ፡፡

ወጣቶቹ በቤተ መንግሥቱ የጣሉት አደጋም ፋሺስቶች በኢትዮጵያ ሰፍኗል ያሉት ጸጥታና ሰላም የይስሙላ እንደነበረ ለመላው ዓለም ከማሳየቱም በላይ ለኢጣሊያውያን የዳር አገሩ ብቻ ሳይሆን መሐሉም ጭምር አደገኛ መሆኑን ያሳዩበት ተጨባጭ ምሳሌ ሆኗል፡፡ ምንም እንኳ ለዚህ አደጋ በፋሺስቶች በኩል የተሰጠው ምላሽ ፍጹም ጭካኔ የተሞላበት ቢሆንም፤አብርሐም ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም የጣሉት አደጋ በአምስቱ ዓመት ጸረ ፋሺስት ትግል መዘክር ውሥጥ በጠላት አመራር ላይ በቅርብ የደረሰ ብርቱ ጥቃት ተደርጎ ስለሚወሰድ ታሪክ ለዘላለም ሲያስታውሰው ይኖራል፡፡

No comments:

Post a Comment