Saturday, October 5, 2013

ቀጣዩ የኢሕአዴግ ዒላማ ማኅበረ ቅዱሳን ይኾን?

ቀጣዩ የኢሕአዴግ ዒላማ ማኅበረ ቅዱሳን ይኾን?


(ፋክት መጽሔት፤ ቁጥር 14 መስከረም ፳፻፮ ዓ.ም.)






ተመስገን ደሳለኝ

የኢሕአዴግ ታጋዮች የመንግሥት ‹‹ጠንካራ ይዞታ›› የሚባሉ ከተሞችን ሳይቀር መቆጣጠር ችለዋል፤ ወደ አዲስ አበባም የሚያደርጉት ግሥጋሴም ፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያምን ሳይቀር ዕንቅልፍ ነስቷል፡፡ በአንዳች ተኣምር ግሥጋሴውን መግታት ካልቻሉ በጥቂት ወራት ውስጥ ሁሉም ነገር ታሪክ እንደሚኾን በማወቃቸው መላ በማፈላለጉ ላይ ተጠምደዋል፡፡ በዚህን ጊዜ ነበር(የሐሳቡ አመንጪ ተለይቶ ባይታወቅም)፣ ‹‹ለዩኒቨርስቲ ተማሪዎች አጭር ሥልጠና ሰጥቶ ከሀገሪቱ ሠራዊት ጎን ማሰለፍና የ‹ወንበዴውን ጦር› ማድረሻ ማሳጣት›› የሚለው ሐሳብ እንደ መፍትሔ የተወሰደው፡፡

እናም መንግሥቱ ራሳቸው ተማሪዎቹን በዩኒቨርስቲ አዳራሽ ሰብስበው እንዲህ ሲሉ አፋጠጧቸው፡- ‹‹እነርሱ (ኢሕአዴግና ሻዕቢያን ማለታቸው ነው) ለእኵይ ዓላማቸው ከእረኛ እስከ ምሁር ሲያሰልፉ እናንተ ምንድን ነው የምትሠሩት? በሰላማዊ ሰልፍና በስብሰባ ብቻ መቃወም ወይስ ወንበዴዎቹ እንዳደረጉት ከአብዮታዊ ሠራዊታችነ ጎን ቆማችኹ የአገሪቱን ህልውና ታስከብራላችኹ?››

ይህን ጊዜም አስቀድሞ በተሰጣቸው መመሪያ ከተማሪው ጋራ ተመሳስለው በአዳራሹ የተገኙት የደኅንነት ሠራተኞችና የኢሠፓ ካድሬዎች ‹‹ዘምተን ከጠላት ጋራ መፋለም እንፈልጋለን›› ብለው በስሜትና በወኔ እየተናገሩ በሠሩት ‹ድራማ› ተማሪው ትምህርት አቋርጦ እንዲዘምት ተወሰነ፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲም ተዘጋ፤ ተማሪዎቹም ለወታደራዊ ሥልጠና ደቡብ ኢትዮጵያ ወደሚገኘው ብላቴ የአየር ወለድ ማሠልጠኛ ከተቱ፡፡

ከመላው ዘማቾች ዐሥራ ሁለት የሚኾኑ ተማሪዎች ተሰባስበው ሲያበቁ በየቀኑ ካምፓቸው አቅራቢያ ወደሚገኘው ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በመሄድ ከመዐቱ ይታደጋቸው ዘንድ ፈጣሪያቸውን በጸሎት መማጠን የሕይወታቸው አካል አደረጉት፤ ከቀናት በኋላም በአንዱ ዕለት አንድም ለመታሰቢያና ለበረከት. ሁለትም ስብስቡ ሳይበተን ወደፊት እንዲቀጥል በሚል ዕሳቤ ‹‹ማኅበረ ሚካኤል›› ብለው የሠየሙትን የጽዋ ማኅበር መሠረቱ፡፡ . . . ይኹንና ከመካከላቸው አንዳቸውም እንኳ በ፲፱፻፸፯ ዓ.ም በፓዌ መተከል ዞን የተደረገውን የመልሶ ማቋቋም ሠፈራ ፕሮግራም እንዲያመቻቹ በዘመቱ ተማሪዎች ከተመሠረተውና ከተለያዩ የጽዋ ማኅበራት ጋራ በመዋሐድ የዛሬውን ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን›› እንደሚፈጥሩ መገመት የሚችሉበት የነቢይነት ጸጋ አልነበራቸውም፤ የኾነው ግን እንዲያ ነበር፡፡



ማኅበረ ቅዱሳን

የ‹‹ማኅበረ ሚካኤል›› መሥራቾች ከተማሪ ጓደኞቻቸው ጋራ ‹‹ይለያል ዘንድሮ የወንበዴ ኑሮ››ን እየዘመሩ የገቡበት ወታደራዊ ሥልጠና ተጠናቅቆ ወደ ጦር ሜዳ ከመግባታቸው በፊት ዐማፅያኑ አሸንፈው የመንግሥት ለውጥ በመደረጉ ሥልጠናቸውን ሳይጨርሱ ወደየመጡበት ተመለሱ፡፡ ኾኖም ለውጡ በተካሄደ በዓመቱ እነርሱን ጨምሮ በአምላካቸው፣ በጻድቃን፣ በሰማዕታትና በመላእክታት ስም የተመሠረቱ[ከአቡነ ጎርጎርዮስ ዘንድ ሲማሩ የቆዩ] የተለያዩ ማኅበራት ተሰባስበው ወደ አንድ እንዲመጡ መደረጉ ሊጠቀስ የሚገባ ልዩነት ባይፈጥርም ስያሜው ግን ብርቱ ክርክር አሥነሳ፤ አቡነ ገብርኤልም ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን ብዬዋለኹ›› ብለው ውጥረቱን አረገቡት፡፡ ዕለቱም[ልደቱን የሚቆጥርበት] ግንቦት ፪ ቀን ፲፱፻፹፬ ዓ.ም. እንደነበር ተጽፏል፡፡

ዓላማው ምንድን ነው?


ማኅበረ ቅዱሳን ሲመሠረት ዓላማዬ ብሎ የተነሣበት መሠረታዊ ጉዳይ በተለያየ ጊዜ ለኅትመት ባበቃቸው ድርሳናቱ ተገልጧል፡፡ እርሱም፡-ትምህርተ ሃይማኖት፣ ሥርዐተ እምነት፣ ክርስቲያናዊ ትውፊትና ታሪክ ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ ማስቻል ነው፡፡

ማኅበሩ ከመሰሎቹ የተለየ ጥንካሬ እንዲኖረው ያስቻለው ዓላማውን ከግብ ለማድረስ በዋናነት በሀገሪቱ የተለያዩ ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች የሚማሩ ተማሪዎችን አባል ማድረጉ ላይ ተግቶ መሥራቱ ነው፡፡ ዛሬም ድረስ መስፈርቱ እያገለገለ እንደኾነ ይታወቃል፤ ይህ ኹኔታም ይመስለኛል አንዳንድ ጸሐፍት ማኅበሩን ‹‹ቤተ ክርስቲያኗ በዩኒቨርስቲዎች ያላት እጅ›› እንዲሉት ያስገደዳቸው፡፡

የኾነው ኾኖ ማኅበሩ በምሥረታው ማግሥት በሃይማኖቱ የመጨረሻውን ሥልጣን በያዘው ቅዱስ ሲኖዶስ ዕውቅና ተሰጥቶት በጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ ሥር እንዲኾን ተደረገ፡፡ በ፲፱፻፹፭ ዓ.ም. ደግሞ መተዳደርያ ደንቡን አጸደቀ፡፡

የግጭት ጅማሬ

. . . አንዳንድ የኢሕአዴግ አመራሮች በብላቴ ከተመሠረተው ‹‹ማኅበረ ሚካኤል›› ጋራ በማያያዝ የማኅበሩን መሪዎች አልፎ አልፎ ‹‹ተረፈ ደርግ›› እና ‹‹መአሕድ›› እያሉ ከማሸማቀቅ ባለፈ ብዙም ጫና አያደርጉባቸውም ነበር፡፡ ዛሬ ማኅበሩን በመንግሥት ጥቁር መዝገብ በቁጥር አንድ ጠላትነት እንዲሰፍር ካደረጉት ልዩነቶች(ያለመግባባቶች) መካከል ዋናዎቹን በአዲስ መሥመር እጠቅሳለሁ፡፡

ኢሕአዴግ የአገሪቱን ምሥረታ ከዐፄ ምኒልክ ዘመን የሚጀምር የመቶ ዓመት ማድረጉ ማኅበሩ ዓላማዬ ከሚለው ‹‹ታሪክን ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ›› ጋራ መታረቅ አለመቻሉ ያስከተለው ውጥረት የመጀመሪያው ነው፡፡ ማኅበሩ ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ታሪክ 2000 ዓመት ወደኋላ ሄዶ ማስላቱ ብቻውን፣ ‹‹አንዲት ኢትዮጵያን በመፍጠር ስም ምኒልክና ተከታዮቹ ያስፈኑትን ጭቆና በጠመንጃ ለማስወገድ በረሓ ገባን›› ከሚሉት የህወሓት መሥራቾች ጋራ ሊያጋጨው መቻሉ የሚጠበቅ ነበር፡፡ ጉዳዩን ከለጠጥነው ደግሞ ‹‹ማኅበሩን በ1980ዎቹ አጋማሽ እንደ ስጋት ይመለከተው የነበረውን ‹የሸዋ ፊውዳል› ወደ ሥልጣን ለማምጣት ያደፈጠ ተቃናቃኝ አድርጎ ፈርጆት ነበር›› ወደሚል ጠርዝ ሊገፋን ይችላል፡፡ በነገራችን ላይ፣ በፖሊቲካው መንገድ ለሹመት የበቁት አቡነ ጳውሎስም እስከ ኅልፈታቸው ድረስ ማኅበሩ በሸዋ ተወላጅ ጳጳስ ሊተካቸው የሚያሤር ይመስላቸው እንደነበር ይነገራል፡፡

በጥቅሉ በኢሕአዴግና በማኅበረ ቅዱሳን መካከል የርእዮተ ዓለም (በብሔር እና በኢትዮጵያዊነት ላይ የተመሠረተ) ልዩነት መኖሩ ላለመግባባቱ መነሾ ነው፡፡

ሌላው የቅራኔአቸው መንሥኤ፣ በወርኃ ሚያዝያ ፲፱፻፺፫ ዓ.ም ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያምና ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ጋራ ሰብአዊ መብትንና አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት ባደረጉ ማግሥት፣ በዋናው ግቢ ከተቀሰቀሰው ተቃውሞ ጋራ የሚያያዘው ኹነት ነው፡፡ በወቅቱ ተማሪዎቹ በሰላማዊ መንገድ ላቀረቡት ጥያቄ የጸጥታ አስከባሪዎች የኃይል ምላሽ መስጠታቸው ጉዳዩን ከቁጥጥር ውጭ አደረገው፡፡ ድብደባውና ማሠቃየቱ ከአቅም በላይ የኾነባቸው የተወሰኑ ተማሪዎችም ከመንበረ ፓትርያርኩ በአጥር ወደሚለየው ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሸሽተው ይገባሉ፡፡ በአካባቢው የነበሩ የጸጥታ ሠራተኞችም የግቢውን በር ይቆልፋሉ፤ ተማሪዎቹንም በኃይል አስወጥተው ደብድበው አሰሯቸው፤ ድርጊቱንም ማኅበረ ቅዱሳን በስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ የቤተ ክርስቲያኗን ለሸሸ መጠለያነት ታሪክ አጣቅሶ አጠንክሮ መቃወሙ ከመንግሥት ጋራ በዐደባባይ ቅራኔ ውስጥ ከተተው፡፡

ሌላው ቅራኔአቸውን ያጦዘው ክሥተት ደግሞ በአቶ ተፈራ ዋልዋ በ፲፱፻፺፰ ዓ.ም ወርኃ ጥቅምት ‹‹መንግሥትና አብዮታዊ ዴሞክራሲ›› በሚል ርእስ ለዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ሥልጠና በተሰጠበት ወቅት ኦርቶዶክስን ‹‹የነፍጠኞች ምሽግ››፣ ጥምቀቱንም ‹‹በውኃ መንቦጫረቅ›› ብሎ ማጣጣሉ ሲኖዶሱን ግድ ባይሰጠውም፣ ማኅበረ ቅዱሳንን አስቆጥቶ መልስ እንዲሰጥ ያደረገበት ኩነት መፈጠሩ ነበር፡፡

የመዋቅሩ ስፋትና የውጥረቶቹ ጡዘት

የማይቆጣጠረውን የተደራጀ ኃይል አጥብቆ ለሚፈራው ኢሕአዴግ፣ የማኅበሩ መዋቅር እየሰፋ መሄድ ስጋት ላይ ጥሎታል፡፡ አባላቱ የዩኒቨርስቲ ወይም ኮሌጅ ምሩቃን መኾናቸው ከገጠር እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ድረስ የራሱ ሰዎች እንዲኖሩት አድርጓል፡፡ የአገዛዙም ጭንቀት ‹‹ይህ ኃይል አንድ ቀን በተቃውሞ ፖሊቲካ ሊጠለፍ ይችላል›› የሚል ነው፡፡ ይህንንም የሚያረጋግጠው አቶ ኣባይ ፀሃየ መስከረም ፲፪ ቀን ፳፻፪ ዓ.ም. የማኅበሩን አመራር በሲኖዶስ ጽ/ቤት ባነጋገረበት ወቅት ‹‹ኢሕአዴግ ገለልተኛ የሚባል ነገር አይገባውም›› የሚል መኾኑን ስናስታውስ ነው፡፡

. . .በኢሕአዴግና በቅንጅት መካከል በድኅረ ምርጫ – 97 የተፈጠረውን አለመግባባት ቤተ ክርስቲያኗ የቄሣርን ለቄሣር ብላ ለማንም ሳትወግን ዕርቅ እንዲፈጠር መሸምገል እንዳለባት ማኅበሩ በልሳኖቹ መወትወቱ የተገላቢጦሽ አገዛዙን አስኮረፈው፡፡ በአናቱም ከአማራ ክልል የተላከው ሪፖርት፣ ‹‹በገጠር ያሉ የማኅበሩ አባላት ለተቃዋሚዎች ቀስቅሰዋል›› ማለቱ ውጥረቱን አንሮታል፡፡

በሌላ በኩል መንግሥት ለሦስተኛ ጊዜ ባካሄደው የሕዝብ ቆጠራ ‹‹የ[ኦርቶዶክስ]ክርስቲያኑ ብዛት 33 ሚልዮን ነው›› ማለቱ፣ ‹‹45 ሚልዮን ነው [የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያን መረጃ በመጥቀስ ከሚለው ማኅበረ ቅዱሳን ጋራ አለመግባባት ውስጥ ከቶት እንደነበር ይታወሳል፡፡

የኢሕአዴግ ክሦች

ኢሕአዴግ በ፲፱፻፺፱ ዓ.ም በጅማ በሻሻ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ካህናትና ምእመናን ‹‹የእስልምና እምነት ተከታዮች ናቸው›› በተባሉ አንገታቸው በስለት ተቆርጦ መገደላቸውን የሚያሳየውን ፊልም በሲዲ አባዝቶ ያሰራጨውም ኾነ ከጭፍጨፋው ጀርባ የመንግሥት እጅ አለበት የሚል የስም ማጥፋት ዘመቻ የመራው ማኅበሩ ነው ብሎ ያምናል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በአዲስ አበባ ‹‹ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ናት››፣ በጎንደር ‹‹ጎዶልያስ›› (የእግዚአብሔር ጦር) የሚል ጽሑፍ የታተሙባቸው ቲሸርቶች አዘጋጅቶ ያሰራጨው ማኅበረ ቅዱሳን ነው ሲል ይከሳል፡፡ በነሐሴ ወር ፳፻፭ ዓ.ም በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሽፈራው ተክለ ማርያም ስም ‹‹የአክራሪነት/ጽንፈኝነት ዝንባሌዎችና መፍትሔዎቻቸው›› በሚል ርእስ የተሰራጨው ሰነድ ክሡን፡- ‹‹ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ነች፤ አንድ አገር አንድ ሃይማኖት ወዘተ ጉዳዮችን በማቅረብ በአንድ በኩል የሃይማኖት ብዝኃነትን የሚፃረር፣ በሌላ በኩል ደግሞ አገራችን የሃይማኖት ብዝኃነት መኾኗን የሚቃወም አካሄድ ነው፤›› ሲል ያጠናክረዋል፡፡

የኦቦይ ስብሃት ኩዴታ

በ፳፻፩ ዓ.ም ፓትርያርኩ አቡነ ጳውሎስ ከሲኖዶሱ ጠንካራ ተቃውሞ አጋጥሟቸው እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይኹንና ከዚህ ንቅናቄ ጀርባ አቡነ ሳሙኤልና ሁለት የማኅበረ ቅዱሳን አባላትን የያዙት ኦቦይ ስብሃት ነጋ እንደነበሩበት ለጉዳዩ ቅርብ ከነበሩ ሰዎች አረጋግጫለኹ፡፡ አቦይ ስብሃት ‹‹አቡነ ጳውሎስ ለኢሕአዴግ ዕዳ ነው›› ብለው መደምደማቸው ለኩዴታ እንዳነሣሣቸው ይነገራል፡፡

. . .[በተቃውሞው] ውጤት ፓትርያርኩ አሸነፉ፡፡ ማኅበሩ የእንቅስቃሴው ተቃዋሚ መኾኑን የተረዱት አቦይ ስብሃት ነጋ ጥርስ እንደነከሱበት ይነገራል፡፡ በነገራችን ላይ፣ የአቦይ ዕቅድ ቢሳካ ኖሮ ተያይዘው የሚነሡ አለመግባባቶችን በመጠቀም ማኅበሩን መምታትንም የሚያካትት ነበር፡፡

የዋልድባ ጉዳይ

በመንግሥትና በማኅበረ ቅዱሳን መካከል የነበረውን አለመግባባት ወደላቀ ጠርዝ ያደረሰው በዋልድባ ገዳም አካባቢ ይቋቋማል የተባለው የስኳር ፋብሪካ ጉዳይ ነው፡፡ በገዳሙ የሚኖሩ ምእመናንን ጨምሮ በርካታ የእምነቱ ተከታዮች ያሰሙትን ተቃውሞ ችላ በማለት ወደ ሥራ ለመግባት በሞከረው መንግሥት ላይ የተነሣው ተቃውሞ ተጠናክሮ ቀጠለ፡፡ ይኹንና ሥርዐቱ ገዳሙ ላይ አልደርስም ብሎ ሲከራከር፣ ቤተ ክህነትም የማጣራት ሥራ መሥራቱን ገልጦ ‹‹ምንም ዐይነት ችግር የለም›› ብሎ ከመንግሥት ጎን ቆመ፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ጉዳዩን ቦታው ድረስ ሄዶ የሚያጣራ አምስት አባላት ያለው ቡድን ወደ ዋልድባ ላከ፡፡ ቡድኑ አጥንቶ ባቀረበው ሪፖርት፡- ‹‹16.6 ሄክታር መሬት ከገዳሙ ተወስዷል፤ ገዳሙን የውኃ መጥለቅለቅ ያሰጋዋል፤ . . .›› የሚል ሪፖርት ለመንግሥት አቅርቧል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ የዶ/ር ሽፈራው ሰነድ የማኅበሩን ጥናት እንዲህ ሲል ኮንኖታል፡- ‹‹መንግሥት በሃይማኖታችን ጣልቃ ገብቷል በሚል ገሃድ ፍላጎትና ድብቅ አሠራር ካላቸው የውጭ ቡድኖች ጋራ በማበር ሰላምን አደጋ ውስጥ የማስገባት፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዐቱን በሃይማኖት ሽፋን ለመናድ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ በቅርብ በነበረው የፓትርያርክ ምርጫና በዋልድባ ገዳም ዙሪያ የተፈጠረው ዝንባሌ የነዚህ ፍላጎቶች ማሳያ ነው፡፡››

የፓትርያርኩ ኅልፈት

በ፳፻፬ ዓ.ም መጨረሻ አቡነ ጳውሎስ ማለፋቸው ሌላ ፍጥጫን አስከትሏል፡፡ ማኅበሩ ስደተኛውን ፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስን ከአሜሪካ አምጥቶ ወይም እንዳሻው የሚያሽከረክረውን ጳጳስ መንበሩ ላይ ለማስቀመጥ ምርጫው በሚፈልገው መንገድ እንዲጠናቀቅ በርትቶ እየሠራ ነው የሚለው ወቀሳ የመንግሥት ቁጣን የበዛ አድርጎታል፡፡ የጠቀሱት ሰነድም ውንጀላውን በገደምዳሜ ገልጾታል፡- ‹‹በእስልምናም ይኹን በክርስትና ሃይማኖቶች ሽፋን የሚደረገው የአክራሪነት/ጽንፈኝነት እንቅስቃሴ በዋናነት እየነጣጠረ የሚገኘው የተቋማቱን የበላይ አመራር ዕርከኖች መቆጣጠር ነው፡፡››

ናዳው እየመጣ ነው?

ባለፉት ሁለት ዓመታት የእስልምና እምነት ተከታዮች ‹‹መንግሥት በሃይማኖታችን ጣልቃ አይግባ›› በሚል የጀመሩትን ትግል ተከትሎ አገዛዙ ማኅበረ ቅዱሳንንም ደርቦ የመምታት ዕቅድ እንዳለው የሚጠቁሙ ምልክቶች ታይተዋል፡፡ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤትን በሚኒስትር ማዕርግ የሚመራው አቶ ሬድዋን ሑሴን፣ ‹‹መንግሥት ጉዳዩን በሰላም ቢጨርሰው የተሻለ ነው›› ሲሉ ምክር ለመለገሥ ለሞከሩ የምዕራብ አገሮች ዲፕሎማቶች፣ ‹‹የአወሊያን ቡድን በዚህ መልኩ ሳናበረክከው ቀርተን መጅሊሱን እንዲወስድ ብናደርግ፣ ነገ ደግሞ ማኅበረ ቅዱሳን ‹ሲኖዶሱን አምጡ› ቢለን ምን መለስ ይኖረናል?›› ሲል የሰጠው ምላሽ ይህንኑ የሚመለክት ነው፡፡

የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር መ/ቤት ባለፈው ዓመት ወርኃ የካቲት ‹‹ለሃይማኖት ተቋማት የተዘጋጀ›› ብሎ ያሰራጨው ሰነድ ማኅበረ ቅዱሳን እና መብታቸው እየጠየቁ ያሉ የእስልምና እምነት ተከታየች የጥቃቱ ዒላማ እንደኾኑ ያሳያል፡፡ ሂደቱን በመምራትም ኾነ በማስፈጸም ከፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር ጀርባ ኾኖ በዋናነት የሚሠራው የፀረ ሽብር ግብረ ኃይል እንደኾነ ይታወቃል፡፡ ዶ/ር ሽፈራው ተክለ ማርያም ‹‹የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የፖሊቲካ ርብርብ ሜዳ አይኾኑም፤ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችም ከማንኛውም ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ ነጻ መኾን አለባቸው›› ያሉበት ዐውድ ‹‹በዩኒቨርስቲዎች የአካዳሚ ትምህርትን ተገን በማድረግ እምነትን ማስፋፋት አይቻልም›› በማለት ማኅበሩ እንደ ቀድሞው አባላቱን ለማስተማር የሚችልበትን ኹኔታ የሚያግድ ነው፡፡

በ፳፻፮ ዓ.ም በዩኒቨርስቲዎች ይተገበራል የሚባለው አለባበስንና አመጋገብን የሚመለከተው መመሪያም ራሱን የቻለ አደጋ አለው፡፡ እንዲሁም የሃይማኖት ማኅበራት ዓላማቸውን አሳውቀው እንዲመዘገቡ የሚያስገድደውን ሕግ በምክር ቤት ለማጸደቅ ዝግጅቱ ተጠናቋል፡፡ መዝጋቢው ክፍል ማኅበራቱን በፍርድ ቤት ከማስቀጣት እስከ ማፍረስ የሚያደርስ ሥልጣን እንደሚሰጠው ምንጮቼ መረጃ አድርሰውኛል፡፡ ይበልጥ የመንደነግጠው ደግሞ በዚህ መልክ ማኅበራቱን ከጠለፉ በኋላ ማንም ሰው ‹‹ቅዱስ ቃሉን›› ለመስበክ ፈቃድ ማግኘትን ግዴታ ለማድረግ መታቀዱን ስናነብ ነው፡-

‹‹የሰባክያን/ዳኢዎች ሚናን የበለጠ ለማጎልበትና የተጠያቂነት ሥርዐት ለመትከል እያንዳንዱ የሃይማኖት ተቋም የራሱን መምህራን የሚለይበትን የመታወቂያ ሥርዐት ሊያበጅና በዚህም የክትትል ሥራ እንዲሠሩ መደገፍ ይቻላል፡፡››

ሰነዱ ወደ መንፈሳዊ ኮሌጅ የሚገቡ ተማሪዎችንም መልምሎ የሲኖዶሱን፣ የማኅበረ ቅዱሳንን፣ የመጅሊስን. . .አመራርነት የመያዝ ዕቅድ እንዳለው በዘወርዋራ ይጠቁማል፡፡ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር በ፳፻፬ ዓ.ም ባዘጋጀው የሥልጠና ማንዋል ላይም ‹‹በኦርቶዶክስ ክርስትና መድረክ አክራሪው ኃይል ማኅበረ ቅዱሳን ነው›› ሲል መፈረጁ ይታወሳል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም የማኅበረ ቅዱሳንን ግቢ ጉባኤ በማዳከም፣ ከሰንበት ት/ቤቶች፣ ከሰበካ ጉባኤና ከሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች ጋራ በማጋጨት፣ በካህናት በማስወገዝና በመሳሰሉት ተጠቅሞ ሊያፈርሰው እንደተዘጋጀ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በጥቅሉ ሰነዱ ማኅበረ ቅዱሳንን ‹‹በሃይማኖት ሽፋን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት መንግሥታዊ ሃይማኖት መኾን ይገባዋል በሚል በአቋራጭ በአቋራጭ የፖለቲካ መሣርያ ለማድረግ የሚንቀሳቀስ›› ሲል ይኮንነዋል፡፡ ‹‹የአክራሪነትና ጽንፈኝነት ምንጩን ለማድረቅ እየተሠራ የሕግ የበላይነትን የማስከበር ሥራም ጎን ለጎን መፈጸም ያለበት ነው፤›› ሲል ጥቁምታ ይሰጣል፡፡

መፍትሔው ምንድን ነው?

ከላይ በጥቅሉ እንደጠቀስኩት የ22 ዓመታቱ ሂደት የሚያስረግጠው፣ የኢሕአዴግን ማንኛውም ዓለማዊም ኾነ ሃይማኖታዊ ተቋማት ነጻነት ያለማክበሩ ብቻ ሳይኾን ቀስ በቀስ ህልውናቸውን ለዘላለሙ ለማጥፋት በሙሉ ኃይሉ እየሠራ እንደኾነ ነው፡፡

. . . ማኅበሩ ዝምታውን በመግራት የራሱን ህልውና እጅግ በፍጥነት ለመታደግ መሞከር ይኖርበታል፡፡ ከሥርዐቱ የፖሊቲካ ዘዬ እንደተረዳነው ቀስ በቀስ እየተረዳነው በመጣው አፈና ላይ ማኅበሩ አንገቱን ቀብሮ፣ ጣልቃ ገብነቱን ቸል ብሎ የማንገራገሩ አካሄድ፣ በአንድ ክፉ ቀን በመጅሊሱ የተፈጸመው ታሪክ በራሱም ላይ መደገሙ አይቀሬ እንደኾነ ለመናገር ነቢይ መኾንን አይጠይቅም፡፡ የትምህርት ተቋማትን የረገጡ ከተሜ ወጣቶች በማኅበሩ ውስጥ መብዛታቸው የመውጫ መንገዱን በአመራሩ ላይ ይጥለዋል፤ ‹‹ለትላንት አናረፍድም፤ ለነገ አንዘገይም›› እንዲሉ የቤተ ክርስቲያኗ ሊቃውንት፡፡

ማስታወሻ፡- ጽሑፉ ከአንዳንድ መረጃውና ይዘቱ አንጻር መጠነኛ አርትዖት ተደርጎበት የቀረበ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment