Monday, January 28, 2013

የፖለቲካ እሥረኞች ይፈቱ’ የሚል ሠልፍ ዋሽንግተን ውስጥ በኦሮሞ ተወላጆች ተካሄደ

ከአቶ በቀለ ገርባ እና ከአቶ ኦልባና ሌሊሣ በተጨማሪ በስም የተጠቀሱት ወልቤካ ለሚ፣ አደም ቡሣ፣ ሃዋ ዋቆ፣ ሞሐመድ መሉ፣ ደረጀ ከተማ፣ አዲሱ ምክሬ እና ገልገሎ ጉፋ በእሥር ላይ እንደሚገኙ የሠልፉ አስተባባሪዎች ተናግረዋል፡

የኦሮሞ ተወላጆች ሠልፍ በዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት

ሰላማዊ ሠልፉን ያዘጋጁት የኦሮሞ ጥናት ማኅበር፣ በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢዋ የኦሮሞ ማኅበረሰብ ድርጅት፣ የኦሮሞ ወጣቶች ራስ አገዝ ማኅበር፣ የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብቶች ሊግና የኦሮሞ ድጋፍ ቡድን ናቸው፡፡
ሠልፈኞቹ ባለስምንት ነጥብ ጥያቄአቸውን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በፅሁፍ ያስገቡ ሲሆን በአደባባዩ ላይም እነዚህን ጥያቄዎቻቸውን የያዘውን ለዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂላሪ ክሊንተን በስም የተፃፈውን ደብዳቤ የኦሮሞ ጥናቶች ማኅበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ሞሲሣ አጋ ሙሉውን በንባብ አሰምተዋል፡፡
ስምንቱ ጥያቄዎቻቸው፡- የኢትዮጵያ መንግሥት አቶ በቀለ ገርባን፣ አቶ ኦልባና ሌሊሣን፣ እንዲሁም ሌሎቹንም ሰባት የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑ በፖለቲካ ምክንያት ተይዘው የረዥም ዓመታት እሥራት የተፈረደባቸውን ሰዎች ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ እንዲፈታ ዩናይትድ ስቴትስ ብርቱ አቅም ያለውን የፖለቲካ፣ የምጣኔ ኃብትና የዲፕሎማሲ ጫናዋን እንድታሣድር፤
የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ መንግሥት የኢትዮጵያን ሕገመንግሥት እንዲያከብር፣ ከፍርድ ውጭ የሆኑ ግድያዎችንና ንፁሃን ሰዎችን ያለክሥ ለተራዘመ ጊዜ ማሠሩን እንዲያቆም የአሜሪካ መንግሥት ምክር እንዲሰጥ፤
ዩናይትድ ስቴትስ ለኢትዮጵያ የምጣኔ ኃብት ድጋፍ ከመስጠቷ በፊት የፖለቲካ እሥረኞች ሁሉ እንዲፈቱ አስገዳጅ ጫና እንድታደርግ፤
የኢትዮጵያ መንግሥት የኦሮሞን ሕዝብና የሌሎቹንም ሰብዓዊ መብቶች፣ ሃሣብን የመግለፅና የመደራጀት ነፃነቶችን እንዲያከብር አሜሪካ እንድትጠይቅ፤

የኢትዮጵያ መንግሥት መሠረታዊ የሆኑ የዜጎችን መብቶች የሚጥሱ አዳዲስ ሕግጋትን ሁሉ፣ በተለይ ፀረ-ሽብር የሚባለውን ሕጉን፣ የፕሬስ ሕጉን፣ የረድዔት ድርጅቶች በሃገሪቱ ውስጥ እንደልባቸው እንዳይንቀሣቀሱ የሚገድበውን የሲቪል ማኅበራት ማቋቋሚያ ሕጉን፣ እንዲሁም ስካይፕንና ሌሎችም የሚድያ አገልግሎት ዘዴዎችን መጠቀምን ሕገወጥ የሚያደርገውን በቅርብ ያወጣውን ሕጉን እንዲሠርዝ የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት እንዲጠይቅ፤የኢትዮጵያ መንግሥት ሕገወጥ የሆነው የኦሮሞ ልጆችን ከይዞታዎቻቸው ማፈናቀልና መሬቶቻቸውን መሸጥ በአፋጣኝ እንዲያቆም አሜሪካ እንድትጠይቅ፤

መንግሥቱ የሃይማኖት ነፃነትን እንዲያከብር እና በሃይማኖታዊ ጉዳዮች ውስጥም ጣልቃ መግባት እንዲያቆም የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት እንዲጠይቅ የሚሉ ናቸው፡፡

በሁለቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎች ላይ እሥራቱ በተካሄደ ጊዜ አቶ ኦልባና ሌሊሣ የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ ፓርቲ ቢሮ ላፊ፣ አቶ በቀለ ገርባ ደግሞ የኦሮሞ ፌደራሊስት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ሊቀመንበርና የመድረክ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ነበሩ፡፡

አቶ ኦልባና ሌሊሣና አቶ በቀለ ገርባ የተያዙት ‘እኛ ካነጋገርናቸው በኋላ ነው’ ሲሉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቹ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ አጥኚና መርማሪ የነበሩት ክሌር ቤስተን እነ አቶ ኦልባና በታሠሩ በአምስተኛው ቀን ለቪኦኤ ተናግረው ነበር፡፡
ያኔ ኢትዮጵያ ውስጥ በይፋ ፍቃድ ተሰጥቷቸው ሥራ ላይ የነበሩት የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሰዎች ባልተገለፀላቸው ምክንያት በአፋጣኝ ሃገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ መታዘዛቸውንና መውጣታቸውን ክሌር ቤስተን ተናግረው ነበር፡፡

በወቅቱ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር አባላት ናቸው የተባሉ ብዙ ሰዎች መታሠራቸውን የኢትዮጵያ መንግሥትም አልሸሸገም፡፡ የታሠሩት ግን ‘በሕገወጥ ወይም በሽብር ተግባራ ላይ በመገኘታቸው ነው’ ነው የሚለው፡፡ ያኔ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ መለስ ዜናዊ ከነ አቶ ኦልባና መያዝ ጥቂት ቀደም ብሎ ለተወካዮች ምክር ቤቱ ባደረጉት ንግግር ይህንኑ አጠንክረው ተናግረዋል፡፡

የእነአቶ ኦልባና እሥራት እንደተፈፀመ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽንስ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ሺመልስ ከማል በሰጡት መግለጫ አንደኛው የታሠሩት በሽብር ፈጠራ ምከንያት ከታገደው ኦነግ ጋር አላቸው በተባለ ግንኙነት መሆኑን ተናግረው ነበር፡፡ ኅዳር 2005 ውስጥ ተከሣሾቹ እነ አቶ ኦልባና ሌሊሣ እና በቀለ ገርባ የረዥም ዓመታት እሥራት ቅጣት ተፈርዶባቸዋል:::
ዓርብ፣ ጥር 17 ቀን 2005 ዓ.ም በዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የተካሄደውን ዓይነት ተመሣሣይ ሠልፍ ለንደንም ላይ መካሄዱን አስተባባሪዎቹ ተናግረዋል፡

Source  Voa  Amharic





No comments:

Post a Comment