Wednesday, January 16, 2013

የባለራዕይ ወጣቶች ማህበር ፀሀፊ በድህነት ኃይሎች ጉዳት ደረሰብኝ አለች

የባለራዕይ ወጣቶች ማህበር ፀሀፊ በድህነት ኃይሎች ጉዳት ደረሰብኝ አለች
የባለራዕይ ወጣቶች ማህበር የጉለሌ ክ/ከ ፀሀፊ የሆነችው ወጣት ወይንሸት ስለሺ የዛሬ ሳምንት ማክሰኞ ከምሽቱ 12፡30 ሲሆን አፍንጮ በር አካባቢ ከሚገኘው የማህበሩ ፅ/ቤት ለመድረስ 50 ሜትር ሲቀራት በደህንነት ሀይሎች ተይዛ አንድ ሌሊት ሙሉ አካላዊና ስነ ልቦናዊ ጉዳት አንደደረሰባት ለዝግጅት ክፍላችን አስታወቀች፡፡
በማህበሩ ፅ/ቤት ዘወትር ማክሰኞ የሚደረገውን የመማማሪያ ፕሮግራም ለመሳተፍ እየሄደች ሳለ በፅ/ቤታቸው አቅራቢ መንገድ ዳር ጠብቀው አንገቷ ስር መርፌ ከወጎት በኃላ እራሷን ስትስት መኪና ውስጥ በማስገባት አቃቂ ቃሊቲ በሚገኘው አንድ ስውር ቪላ ቤት ግቢ ውስጥ በማስገባት ከብርሀኑ ነጋ ጋር ግንኙነት አላችሁ ከውጭ ሀገር የሚደግፋችሁ ማን ነው የሚሉ የተለያዩ ጥያቄዎችን አቅርበው በሰጠችው ምላሽ ባለመደሰታቸው በጥፊ መመታቶን ገልፃ ለጠየቆት ጥያቄ እውነቱን አውጪ በማለት ግራ እግሯን በመጋረጃ ብረት በመምታት ጉዳት ያደረሱባት ሲሆን በኤሌክትሪክ ንዝረትም ጀርባዋ ላይ የከፋ ጉዳት እንደደረሰባት ገልፃ የህክምና ውጤቷን በመጠባበቅ ላይ መሆኗን ለዝግጅት ክፍላችን አስታውቃለች፡፡
ለስራ የምትጠቀምባቸውን ሁለት ቴፕ ሪከርደሮች (ዲጂታልና አናሎግ) የቤተሰብ ሁለት ሺ አንድ መቶ ሃምሳ ሰባት ብር እና ሞባይል ስልክዋንም እንደወሰዱባት አስታውቃለች፡፡
ወይንሸት ስለሺ እባላለው የጉለሌ ክ/ከ የባለራዕይ ወጣቶች ማህበር ፀሀፊ ነኝ ፡፡በግሌ የደረሰብኝ ማክሰኞ ታህሳስ 30 ቀን 2005 ዓ/ም ማታ ከምሽቱ 12፡30 ሰዓት ላይ ዘወትር በማህበሩ እምናደርገው የውይይት ጊዜ አለን፡፡በዚህ ውይይት ላይ ለመገኘት ሽሮ ሜዳ አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቴ ወደ አፍንጮ በር የሚገኘው የማህበራችን በር ለመድረስ 50 ሜትር ሲቀረኝ ከለሩን ያላየሁት መኪና ሁለት ሰዎች ይዞ አጠገቤ ቆመ፡፡መንገዱ በጣም ጠባብ ስለነበር ወደ ዳር ወጥቼ ላሳልፈው ዘወር ስል አንገቴ ስር መርፌ ወጉኝ እና እራሴን አስተውኝ በመመኪና ውስጥ ጎትተው እስከሚያስገቡኝ ጊዜ ድረስ ብቻ ነውየማውቀው፡፡
ከዛ በኃላ ይዘውኝ ሲሄዱ እራሴን አላውቅም ነበር፡፤ቃሊቲ አካባቢ ጉራንጉር ውስጥ ስንደርስ መኪናው ቆመ እራሴን ያወኩት ከአመራሮቼ ጋር ስልክ ሲደዋወሉ ነበር፡፡እነሱን በጣም አስደንግጠው ሲረበሹ ከቆዩ በኃላ ነው እኔ የነቃሁት፡፡ ስነቃ አንደኛው ሰው እሺ ባለራዕይ ነቃሽ አለኝ፡፡ እሺ ምን ፈልጋችሁ ነው አልኩት፡፡በወቅቱ የወጉኝ መርፌ ማጅራቴንና ጭንቅላቴን ይዞኝ ስለነበር አይኑን በደንብ ገልጬ ማየት አልቻልኩም፡፡ራሴን ከብዶኝ ነበር የሆነ የተቀዳ ድምፅ አሰሙኝ፡፡ ሀብታሙ ስለ ባለዕራዩ ነው የሚያወራው ከዛ የማላውቀው ድምፅ አሰሙ ይህ ድምፅ የብርሀኑ ነጋ ድምፅ ነው፡፡ከሱ ጋር ንግግር ያደረጉት ድምፅ ነው ተቀርፆ የመጣ ነው፡፡ስለዚህ ከግንቦት 7 ጋር ህብረት አላችሁ፤ ስለዚህ ይህን መረጃ ይዘናል፡፡ከዚህ በተጨማሪም ደግሞ የማህበሩ አባላት የእነ ብርሀኑ፣ የሀብታሙ እና ሌሎች አመራሮችን ድንገት ቆመው የተነሱ የሚመስል ፎቶ አውጥተው እሱም የአባልነት ፎቶአቸው መሆኑን ከዛ ያስመጣነው ነው ስለዚህ ያላችሁን ህብረት ተናገሪ አለኝ፡፡
እኛ አሸባሪ ተብሎ ከተፈረጀ ቡድን አይደለም አምነንበትም አልመንበትም ምንም አይነት ህብረት የለንም፡፡ ሀብታሙ ከብርሀኑ ጋር ተደዋውሎ የሚነጋገርበት ጊዜም የለውም የማውቀው ይህንን ነው፡፡ማህበራችነም የፖለቲካ ፓርቲ አይደለም፡፡ሲቪክ ማህበር ነው የሚል ነገር ነው ያስቀመጥኩላቸው፡፡ እና ይሄ የእናንተ ፈጠራ ነው ስለው በጥፊ መታኝ ሁለት ናቸው፡፡ከመኪናው የኃላ ወንበር ላይ ዳር እና ዳር ሆነው መሃል አስቀምጠውኝ ነው የሚያወሩኝ፡፡ሹፌሩ ዞሮም አያየኝም ምንም አይናገርም ፀጥ ብሎ ነው የተቀመጠው ሁለቱ ናቸው የሚያጣድፉኝ፡፡መልካቸውን በደንብ አይቻቸዋለው የትም ቦታ ላይ ባያቸው አውቃቸዋለው፡፡እና በጥፊ እየመቱ አውጪ አሉኝ ምንም አይነት ነገር የለኝም አልኳቸው እኔ የማህበሩን በራሪ ወረቀት አዘጋጅ ስለነበር ጋዜጠኞች የሚጠቀሙበትን ሁለት መቅረፀ ድምፅ ይዣለው፡፡እነርሱም ይህቺን ዲጂታል መቅረፀ ድምፅ ይዛችሁ በየቢሮው እየሰለላችሁ የምትሰሩት ስራ በዚህ ማረጋገጫ አግኝተናል አሉ፡፡ ሁለተኛ ነገር ደግሞ ሁለት ሺ ንድ መቶ ሃምሳ ሰባት የቤተሰብ ብር ይዤ ነበር፡፡ይህን ብር ከሽሮ ሜዳ ሃያሁለት አካባቢ ሄጄ ብሩን ለማድረስ ነበር የያዝኩት፡፡ይህን ብር ወስደው ከውጭ ሀገር የሚላክላችሁ በር ነው እናንተ ያለውጭ ሃገር ድጋፍ ምንም ላይ እንደማትደርሱ እናውቃለን፡፡ስለዚህ ይህ ለእኛ ማስረጃችን ነው ብለው ብሬን ስልኬን እና ሁለት ቴፕ ሪከርዴን ከወሰዱ በኃላ አሁንም አታወጪም እውነቱን ሲለኝ ያለው ነገር ይሄ ስለሆነ ምንም ነገር ልነግርህ አልችልም አልኩት፡፡
በጥፊ ደገመኝና ሹፌሩን ንዳው አለው እና ወደ ውስጥ ዘልቆ ገባ ቦታው በጣም ጨለማ ስለሆነ ዳርና ዳር ያለውን ነገር መለየት አልቻልኩም፡፡ሁለተኛ የደረሰበት አካባቢ ቪላ ቤት ነው ትልቅ ግቢ ነው የውጪው በር ሎሚ ከለር የተቀባ ነው ይህንንም ያየሁት የመኪናውን መብራት ሲያበራው ነው፡፡ ከእኔ በስተግራ በኩል ተቀምጦ የነበረው ወርዶ በሩን ከፈተለትና መኪናው ሲገባ ቤቶች አሉ አንድም ቤት ግን መብራት የበራ የለም ጨለማ ነው፡፡ አንገቴን በእጁ መዳፍ አጥብቆ ይዞ የመኪናው መብራት ጠፍቶ ጨለማ ሆኗል፡፡
እያንደረደረ አንዱ ክፍል ውስጥ አስገቡኝ፡፡በዛ ሰዓት የተሰማኝ ስሜት ሴት መሆኔ በሴትነቴ ተጠቅመው ብዙ ነገር ሊያደርጉኝ ነው የሚል ስጋትም ነበረኝ፡፡ፈራው ግን የፈለገ ነገር ቢመጣ ደግሞ የያዝኩት ዓላማ የወጣቶችን ስብዕና የያዘ መሆኑ በውሸትም ምንም ነገር ማለት አልፈለኩም፡፡
ስለዚህ የፈለጋችሁትን ነገር አድርጉኝ ያለው ነገር ግን ይሄው ነው አልኳቸው፡፡እና ውስጦ ክፍት በሆነችው የመጋረጃ ብረት አንዱ እሱን ይዟል አንደኛው ኤሌክትሪክ ገመድ ይዟል፡፡ቀጥታ በመጋረጃው ብረት ግራ እግሬ ላይ በደንብ አድርጎ ሲመታኝ ተንበረከኩ፡፡
አሁንስ እውነቱን አታወጪም አለኝ የፈለከውን አድርገኝ እኛ ከምንም ጋር ምንም አይነት ህብረት የለንም፡፡ የማውቀው የባለራዕይ ወጣቶች ማህበር ሲቪክ ማህበር እንደሆነ ነው ከዛ የዘለለ ምንም ዓይነት ህብረት አላውቅም አልኩት:: የለበስኩትን ጃኬት አስወለቁኝ እና ቤቱ ሶስት በአራት ያክላል ፣ግድግዳው ሶኬት ብቻ ነው፤መቀመጫ የለውም፡፡ ወለሉ እምነበረድ ነው ግድግዳው ሲሚንቶ ነው በጣም ነው የሚቀዘቅዘው የቤቱ መብራት ማብሪያና ማጥፊያ ከውጪ በኩል ነው ያለው፡፡እና ሶኬት ሰክተው ጀርባዬ ላይ አነዘሩኝ፤ሾከድ አደረጉኝ ፤እየጎተቱ በያዘው ኤሌክትሪክ ሾከድ ያደርገኛል፡፡
በቃ ግደሉኝ አልኳቸው ማረድ ጀምረንሽ ቢሮዋቹ በር ላይ አርደን እንጥልሻለን ከዛ እነሱ ሌሎች አመራሮች ይማሩበታል፡፡እኔን ብትገድሉኝ የእኔ አላማ የሚከተል ብዙ ሺኅ ወጣት አለ፡፡እኔ ግን እዚህ ብዋሽ ብዙ ወጣት ነው ገደል የምከተው ስለዚህ የፈለከውን አድርገኝ አልኩት፡፡እስከ ሌሊቱ 7፡00 ሰዓት ማለት ነው አመራሮች እኔ ስልክ ላይ ሲደውሉ እያነሱ ሲያሾቡባቸው ነበር፡፡ እስከ 7፡00 ሰዓት ሲያሰቃዩኝ ነበር፡፡እንድቆስል እንድደማ ምንም አላደረጉም ምንም የሚታይ ነገር አላደረጉብኝም፡፡
ግን ኤሌክትሪኩ ያደረሰብኝ ነገር አለ፡፡እግሬ ላይ የመቱኝ አብጧል፡፡አንገቴ ላይ የወጉኝ መርፌ እብጠት ይደማ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ካደረጉ በኃላ ሰባት ሰዓት ላይ ከውጭ ቆልፈውብኝ ሄዱ፡፡
ሲሄዱም የሆነ ሀይል ጨምረው እነደሚመጡ አስቤ ጥግ ይዤ ቁጭ ብዬ ጠበኳቸው፤ በዛ ሰዓት በኤሌክትሪክ ሾከድ ያደረጉኝ ፣መርፌ የወጉኝ ፣እግሬ ላይ የመቱኝ ነገር ከቅዝቃዜው ጋር ሲያመኝ አደረ፡፡
ከንጋቱ 12፡00 ሰዓት ላይ ተመልሰው መጡና ለምን አንቺ እውነቱን ነግረሽ አትሄጂም ዱላ ከሚበዛብሽ አሉኝ፡፡ከዚህ በላይ ምንም ልላችሁ አልችልም አልኩ፡፡ ደረቅ ነሽ አለኝ፡፡እኔ የምደርቀው ለእውነት ነው ስላቸው በመለስኩላቸው ቁጥር ያው የተለመደ ምት አለ፡፡በእርግጫም ይሁን ብቻ ደስ ሲላቸው ምት አለ፡፡ግን ጠዋት ላይ ማውራትም አልቻልኩም፡፡ 12፡30 ሲሆን ይዘውኝ ሲወጡ የመኪናውን ታርጋ ማየት እችላለው የሚል ግምት ነበረኝ፡፡
ካልገደሉኝ በስተቀር በቃሌ እይዘዋለው ብዬ ነበር ይዘውኝ ሲወጡ ግን፣ በመዳፉ ዓይኔንና ማጅራቴን ይዞ እያንደረደረ ወደ መኪና አስገባኝ፡፡የመኪናውን ውስጡን እንጂ ውጭውን አላየሁትም፡፡ሰዓቱንም ያየሁት መኪና ውስጥ ከተቀመጥኩበት ፊት ለፊት ሰዓት አለው መኪናውን አዙረው ከጉራንጉር ውስጥ ወጥተን ወደ ዋናው የቃሊቲ መንገድ ወጥተን ቃሊቲ መናህሪያ አካባቢ ስንደርስ ትልልቅ ኮንቴነር ጭነው የቆሙ መኪኖች አካባቢ ላይ መኪናውን አስጠግተው አቆሙና በኤኔትሬው መኪና ጀርባ ወስደው ራቅ አድርገው የሆነ ድንጋይ ላይ አስቀመጡኝና ቢፈልጉ መጥተው ይውሰዱሽ አሉኝ፡፡
የወሰዱብኝን ሁሉ ሳይመልሱልኝ አስቀመጡኝ፡፡የሚገርመው ይህን ያህል ብር እሷ እጅ መገኘቱ እሷ ማን ስለሆነች ነው ብለው ለአመራሮቼ በራሴ ስልክ መልዕክት አስተላልፈውላቸዋል፡፡ያለምንም ነገር ባዶዬን እዛ ድንጋይ ላይ አስቀመጡኝ፡፡መኪናውን ፊት ለፊት ቢያቆሙት እንኳን እኔ ተነስቼ ታርጋ የማየት አቅም አልነበረኝም፡፡በወቅቱ አስከ አራት ሰዓት ተኩል ድረስ ከዛ ቦታ ላይ አልተንቀሳቀስኩም፡፡መቆም አልችልም ነበር፡፡መንገደኞች እየመጡ ምን ሆነሽ ነው ሲሉኝ ምንም አልሆንኩም ነበር የምላቸው ማውራትም አልችልም ነበር ማለት ነው የሁሉንም አመራር ስልክ በቃሌ ነው የያዝኩት ግን በዛን ወቅት የሁሉንም ስልክ ጠፋኝ ማስታወስ አልቻልኩም፡፡
በኃላ ላይ ግን የባልደረባዬን የብርሀኑን ስልክ ነው ያስታወስኩት፡፡ትንሽ ሜትር ሄጄ እየተቀመጥኩ እየተንፎቀኩ ሱቅ ላይ ደረስኩኝ ወጋገን ባንክ ፊት ለፊት ያለችው ሱቅ ላ ደውዬ ወይንሸት ነኝ ስለው አየፈለጉኝ ስለነበር የት ነሽ አለኝ ያለሁበትንም ስለማላውቀው ለባለሱቁ ስልኩን ሰጥቼው ምልክቱን በሚገባ ነግሮት ባለሱቁ በሰጠኝ ወንበር ቁጭ አልኩ ወደ 7፡00 ሰዓት አካባቢ ደረሱልኝና ይዘውኝ ወደ ፒያሳ አካባቢ መጡ፡፡አመራሮች ጠቅላላ ሲጠብቁ ስለነበር የተፈጠረውን ነገር ለመናገር አልቻልኩም፡፡የተወሰነች ነገር ነገርኮቸው፡፡ህክምና መሄድ አለብኝ ከዛ በፊት ግን ለፖሊስ ማሳወቅ አለብሽ የሚል አቅጣጫ ከአመራሩ የተቀመጠው ከቀኑ 9፡00 ሰዓት ፖሊስ ጣቢያ የገባው አስከ ምሽቱ 1፡30 ድረስ አቆይተውኛል፡፡
እያንዳንዱ መርማሪ ሙሉ ታሪኬን ይቀበሊና እኔን አይመለከተኝም እሱ ጋር ሂጂ ይለኛል፡፡ሌላውማ ሙሉ ታሪኬን ተቀብሎ እኔን አይመለከትም እሱ ጋር ሂጂ ይለኛል፡፡መጨረሻ ላይ ግን ማውራት አቅም አነሰኝ አልታከማኩማ ምግብ አልበላሁም ስለዚህ ከዚህ በላይ ማውራት አልችልም የሚል ነገር ነው ያሰቀመጥኩላቸው፡፡ወይም አንቀበልም ብላችሁ ሸኙኝ አልኳቸው፡፡ለጃል ሜዳ ፖሊስ ጣቢ መጨረሻ ላይ ግን የመርማሪዎቹ አዛዥ እሱ ቃሌን ከተቀበለ በኃላ ማረጋገጥ ያለበትን ካረጋገጠ በኃላ ቃል ተቀብሎኝ ከምሽቱ 1፡30 አካባቢ ቃል መስጠቱን ጨርሼ ወጣው ፤ህክምና መሄድ እንዳለብኝና የህክምና ውጤት እንዳመጣ ተነገረኝ፡፡ከወጣው በኋላ የካቲት 12 ሆስፒታል እንድሄድ ቢነገረኝም ሆስፒታሉ በዛ ሰዓት ያለ ፖሊስ ማዘዣ ድንገተኛ ብዬ መግባት እንደማልችል አውቃለው፡፡ስለዚህ አመራሮች ያደረጉት ምግብ እንድበላ ነው ያደረጉት፡፡እኔ ግን 22 አካባቢ ወዳለው የእህቴ ቤት ነው የገባሁት ፡፡እቤት ገብቼ ማታ በጣም ስለታመምኩ ህክምና አገኘው ማሰታገሻ መርፌ ተወጋውና ጠዋት የካቲት 12 ሆስፒታል ሄድኩ፡፡አንገቴ ላይ የተወጋሁትን ምርመራ አደረኩኝ፡፡እግሬ ላይ ተመትቼ ያበጠውን አዩ፡፡በኤሌክትሪክ ሾክድ የተደረኩትን ጀርባዬን ዶክተር ካየ በኃላ ያለውን ነገር መዝግበው ውጤት ሰኞ ጠዋት እንደሚሰጠን እየጠበቅን ነው፡፡ከዛ በኋላ ፖሊስ ጣቢያ እንድመጣ ጠይቀውኝ ነበር፡፡ተመልሰሽ ነይ ብለውኝ ነበር፡፡ውጤት ሳልይዝ የምርመራ ውጤት መጠየቂያ የማልይዝ ከሆነ ምን አስኬደኝ በሚልና ስላመመኝ ወደ ቤት ሄድኩ፡፡ይህው ነው፡፡በመንግስት ሀገር በመሀል ከተማ አፈና ይካሄድብናል፤ አሁን ለማን ይሆን አቤት የሚባለው?

                                                                                 
    ዘገባውን ከዚህ ያድምጡ                                                                                                    

No comments:

Post a Comment