Friday, November 1, 2013

ህወሓት አይድንም፤ እያቃሰተ ነው!!!



በጌታቸዉ አረጋዊ የህ.ወ.ሓ.ት ኣባልና የድምፅ ወያነ ጋዜጠኛ «ውራይና » የሚል በትግርኛ ቋንቋ የተዘጋጀ ለአራተኛ ጊዜ በነሃሴ ወር 2005 ዓ/ም የታተመ መፅሄት ስብሓት ነጋ የህ.ወ.ሓ.ት ፈላስፋ ቃለ መጠይቅ ያደረገበት መፅሄት በፅሞና ኣነበብኩት። የመፅሄቱ ዋና ይዘት ‹‹ህ.ወ.ሓ.ት እናድናት›› ነዉ የሚለዉ ስብሓት ነጋ በመፅሄቱ የተካተቱ ብዙ ስንክሳራዊ ሃተታ ተናግሯል ።
አሁን ማለት የፈለግኩት በመፅሄቱ የተካተቱ በሙሉ መልስ ለመስጠት አይደለም፡፡ ምክንያቱም የስብሓትን ስንክሳር መልስ ለመስጠት ከፈለኩ ግዜ አይገኝም መፅሃፍም ሊሆን የሚችል ነዉ። በመሆኑም አለፍ አለፍ በማለት የስብሓትን አንኳር አንኳር ነጥቦች መልስ ለመስጠት እሞክራለሁ።

ሌላ ይህ ፅሁፍ መልስ ለመስጠት የተገደድኩት የ ህ.ወ.ሓ.ት መሪዎች ለትግርኛ ቋንቋ ማዳበርን በትግርኛ ስነ-ፅሁፍ ለማስፋት ብለዉ በፅሁፍ ቢናገሩ እጅጉን የሚደገፍና የትግራይ ህዝብ መስዋእት ነበር። ይህ ደግሞ ማንም ኢትዮጵያዊ ይድግፈዋል፤፤

የ ህ.ወ.ሓ.ት መሪዎች ግን ከረጅም ጊዜ ጀምረዉ ለትግራይ ህዝብ በጠባብነት ለመነሳሳት ሲፈልጉ ወይ መምቻ ሃይል ሊጠቀሙበት ሲፈልጉ የሚናገሩት የሚፅፉበት ኢትዮጵያዊ አጀንዳ እያለና ያለ ትግራይ ህዝብ የሚነገር የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጉዳይ አድርገዉ እንደመናገር ፈንታ በድብቅ ይናገራሉ።

ስብሓት ነጋም በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ሃገራችን ብዙ ደንቃራ ሁኔታዎች ተደቅነውባትና ህዝቡ በብዙ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፖለቲካዊ ችግሮች አጋጥመውት እያሉ ለትግራይ ለአንድ ክልል ከ4-5 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ለብቻዋ የሚወከል ህ.ወ.ሓ.ት ትንሳኤ መተንበይ ሌላዉ የኢትዮጵያ ህዝብና ክልሎች … በሂወት ካሉት በታች ከሞቱት በላይ የሆኑ ህዝቦችና ክልሎች እንደማሰብ ትግራይን ጨምሮ ማለት ነዉ። ለትግራይ ብቻ ማሰብ ለስብሓት ነጋ ጠባብ ሊያስብላቸዉ የሚችል ይመስለኛል።

በሌላ በኩል የስብሓት ነጋ ትንሳኤ ሙዉታን ሲለን የህ.ወ.ሃ.ት ትንሳኤ ሙታን ለመመለስና የህ.ወ.ሃ.ት መሪዎች ከመሰነጣጠቅና ከመክሰም እንዴት እናድነዉ ጭንቀቱ እንጂ የትግራይ ህዝብ ባጠቃላይ የሃገራችን ህዝቦች ብሄር ብሄረሰቦች ከዲሞክራሲና ሰብኣዊ መብቶች ነፃነትና አፈና አስተዳደር እንዴት እናድናት አይደለም ጭንቀቱ፤፤ ይህ ካልኩ በኃላ ወደ መፅሄቱ ላይ የሰፈረዉ አንዳንድ መልስ ለማስቀመጥ እሞክራለሁ።

ስብሓት ነጋ በአሁኑ ጊዜ ያለዉ የህ.ወ.ሓ.ት አመራር ለነዚህ ለአመታት እያጠራቀማቸዉ የቆየ ችግርን በፍፁም ነፃነት በፍፁም አባታዊነት በትክክል ከተረዳቸዉ መረዳትም ያለበት ነዉ።‹‹የ ህ.ወ.ሓ.ት ትንሳኤ ጊዜ ይወስዳል እንጂ ድላችን የማይቀር ነዉ።›› ይላል ውራይና መፅሄት ነሃሴ 2005 ገፅ 4 ሶስተኛ አምድ አዲስ መስመር ሁለት

ስብሃት ነጋ ከእንግዲህ ወዲህ የምናውቀዉ ህ.ወ.ሓ.ት ከነበሩበት ብዙ ችግሮች ሲያሳየዉ የነበረ መገላበጥ የተሳሳቱ ሃገራዊና አህጉራዊ አቋሞች በተለይ ደግሞ በሃገር ሉኣላዊነት የሚመለከት ሃገራዊ ሃላፊነት የጎደለዉ ብዙ ስህተትና ጥቁር ነጥብ ቢሰራ በፀረ-ደርግ የነበረዉ አቋም የኃላ ኃላ ለስልጣኑና የግዛቱን ማስፋፋት ሲል ያመጣዉ አገር አቀፍ አመለካከት ለኢትዮጵያ ህዝብ ለጊዜዉ ከፋሽስታዊ ደርግ አፈና አድኖታል። ተነፃፃሪ ሰላም ያመጣ ይመሰል ነበር ሆኖም ግን የህ.ወ.ሓ.ት አመራርና እሱን እሚመስሉ እሱ የፈጠራቸዉ የህ.ዋ.ሓ.ት ስሪት ፓርቲዎች ልክ ደርግ መጀመሪያ ወደ ስልጣን ሲመጣ ኢትዮጵያ ትቅደም ያለ ምንም ደም እንዳለና ቀስ በቀስ ወታደራዊ ባህሪዉ አገርሽቶበት ፍፁም ለኢትዮጵያ ህዝብ ፋሽስትና ፀረ ህዝብ የሆነዉ የህ.ዋ ሕ.ት መሪዎች የትግራይ ህዝብና ልጆቹ በሃገር ደረጃ ደርግ ከተደመሰሰ ብቻ ነዉ ሰላም፣ ፍትህ፣ ዲሞክራሲ፣ ነፃነት፣ የህግ የበላይነት ይመጣል እያለ በመቶ ሺዎች ዜጎች የሰጡትን ደርግን አስወግዶ ወንበሩን ከተቆናጠጠ በኃላ ትላንትና ሽሮ አለ መረቅ አለ እያለ ወደ እሳት እየማገደዉ የመጣ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከዳ የትግራይ ህዝብ ነበር። ውጤቱ ደግሞ የትግራይ ህዝብ ሳይሆን መላዉ የኢትዮጵያ ህዝብ በአሁኑ ጊዜ አግኝቶት ያለ ምንድነዉ ?

ስደት በየአህጉሩ ተበታትኖ ሞት መታረድ በባህር የአሳ ቀለብ መሆን ሁሉም አይነት መብቶች ማጣት አንድነት መላላት ሉአላዊነቱን መደፈር ነዉ። በተለይ ደግሞ የህ.ወ.ሓ.ት መሪዎች አመራር ትንሳኤ መውታን ካልተረጋገጠ የትግራይ ህዝብ አይኖርም የምትሉት 22 አመት ሙሉ ለውጥ ያላመጣ ችሎታ አሁን በሁሉም ነገር ከፈረጃችሁ በኃላ ‹‹ከገባንበት አዘቅት አውጡን›› ብትሉን አቶ ስብሃት ማን ያምንሃል የትግራይ ህዝብ ለናንተ ተንከባክቦ አምጥቶ ምን ጥቅም አገኘ ። የትግራይ ህዝብ ልጆች ተምረዉ ስራ አጥተዉ የሚላስ የሚቀመስ አጥተዉ የስብሓትና የጓደኞቹ ልጆች ግን ዘር መንዘራቸዉ በቻይና በእንግሊዝ፣ ኣሜሪካ በሌሎች ምእራብ አገሮች ተምረዉ በተቀማጠለ ኑሮ ነዉ የሚኖሩት፤፤ ይህ እኮ የኢትዮጵያ ህዝብ አበጥሮ ያውቀዋል። ስለዚህ በኔ እምነት በአሁኑ ጊዜ ስብሓት እንደ ምትለዉ የ.ህ.ወ.ሓ.ት መሪዎች ትንሳኤ ሙታን በአሁኑ ጊዜ አያስፈልግም፡፡ አዲስ ትውልድ የአዲሱ ትውልድ የህ.ወ.ሓ.ት አመራር ንኪኪ ያልተበላሸ ኢትዮጵያዊ አመራር ያስፈልጋል። ይህ ነዉ ሃቁ።


« ስብሃት ነጋ የህ.ወ.ሓ.ት አመራር እዚህ ግባ የማይባለዉ አቅም ተነስቶ ለትግራይ ህዝብ አሳልፎ እጅጉን ጥልቀት ካለዉ አድሃሪ አሰላለፍ አሸንፎ ለማመን የማይቻል ሃገራዊ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት በመፍጠር ወሳኝ ሚና ተጫውቷል። አሁንም አሁን ያለዉ የህ.ወ.ሓ.ት አመራር የትግራይ ህዝብ በመያዝ ህ.ወ.ሓ.ት አይፈጠርም አንልም። ‹‹በመሆኑ ቅድምና በቅርቡ ከህ.ወ.ሓ.ት ማ/ኮሚቴ የወጡ የህ.ወ.ሓ.ት አመራር ነበር እንደ አዲስ በመደራጀት አሁን ላለዉ ማ/ኮሞቴ የሚያግዝበት መንገድ መፈለግ አለበት ይላል»

‹‹ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ›› ይባላል አይደለ አቶ ስብሃት የህ.ወ.ሓ.ት አመራር 40 አመት ሙሉ ቆይቷል፤፤ ስብሃት ነጋም 39 አመት በአመራር ቆይተሃል በህ.ወ.ሓ.ት ከ1967፣ 1969፣1970 ዓ/ም የነበሩ የህ.ወ.ሓ.ት የሃሳብ ልዩነት በፀረ ዲሞክራሲ የግጭት አፈታት ስብሃትም ነበርክ በ 1982 ዓ/ም አባይ ፀሃዬ ከስልጣን በማውረድ መለስን ወደ ስልጣን ካስወጡ አንዱ አንተ ነበርክ ።በ1993 ዓ/ም ከህ.ወ.ሓ.ት መሰናጠቅ ጋር ተያይዞ ህ.ወ.ሓ.ት በሁለት አንጃ ሲሰናጠቅ አንተም ስልጣን ከያዘዉ አንጃ ጋር ሆነህ ለወጣዉ አንጃ በማውገዝ በዋናነት አንተ ነበርክ። አሁንም በቅርቡ የነበረዉ የህ.ወ.ሓ.ት መተካካት የሚባልም የተኩ ይሁኑ የተተኩ በሁሉም ነገር እዚህ ግቡ የማይባሉ ናቸዉ፤፤ መሪ የነበረ ሲወርድ አንጃ የነበረዉ ነዉ ወንበሩን የያዘዉ፤፤ ስለዚህ ህ.ወ.ሓ.ት ከሲቪል ብቁ መሪ አላፈራም ብቁ ምሁር የማስጠጋት ባህል አልነበረውምና፤፤ በቅርቡ ከህ.ወ.ሓ.ት የወጡ አመራሮች በመሰረቱ የሚበቃቸው ነገሮች ስለያዙ ነዉ እንጂ ስልጣን ጠልተዉ አይደለም፤፤ እነሱ ቢመለሱም እያቃሰተ ያለዉ ህ.ወ.ሓ.ት ሊያድኑት አይችሉም። አቶ ስብሃት ወንበር ብትይዝም አንደኛ ተቀባይነት የለህም፡ ሁለተኛ እድሜዉም ገፍቷል እነርሱም በቅን ይሁን በተንኮል እየሰሩ አቅማቸው ተጨርሷል። ስለዚህ በቅርቡ ከ ህ.ወ.ሓ.ት የተቀነሳችሁ ህ.ወ.ሓ.ት ልታገግም ለማድረግ አትችሉም፤፤ ህ.ወ.ሓ.ት እኮ በስም እንጂ በአካል የለችም ይህ ትክክልኛ ነዉ።

በ 1993 ዓ/ም የተገነጠሉ አንጃዎች በስብሀት አይን እነሱ ከተመለሱ ህ.ወ.ሓ.ት ትነሳለች ነዉ እያለ ያለዉ?

በኔ እምነት የወጡ አንጃዎች አብዛኞቹና የቀረዉ አንጃ የስልጣንና የሃብት ማካበት ልዩነት እንጂ መሰረታዊ የሆነ የህዝብ ጥያቄ አልነበራቸዉም እነዛ የህዝብ ጥያቄ የሃገር ሉአላዊነት አልተከበረም ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች አልተከበሩም በኢኮኖሚ ፖሊሲ፣በፖለቲካዊ አስተሳሰብ(አይዶሎጂ) ልዩነት የነበራቸውና አሁንም ለህ.ወ.ሓ.ት ኢ.ህ.ኣ.ዴ.ግ እየታገሉ ያሉ ከ3 ሰዎች አይበልጡም።

ሌሎች ግን ትላንትና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ወጣት ግቡ እያሉ ወደ ጦርነት እያስገቡ አዲስ አበባ እንደገቡት እንደጥርስ መፋቂያ ተጠቅመዉ የጣሉት አሁን በወጣቱ መስዋእት ስማቸዉ ገኖ በአለም አቀፍ ታዋቂነት አግኝተዉ በንግድ አለም ተሰማርተዉ ከነቤተሰቦቻቸዉ በመላዉ አለም እየናጠጡ ይገኛሉ። በሃገር ውስጥ ያላቸዉ ሃብትም ለዘር መንዘራቸዉ የሚበቃቸዉ ነዉ። ስለዚህ ስብሃት እያልከን ያለሀዉ እነዚህ አንጃዎች ተመልሰዉ ወደ ህ.ወ.ሓ.ት ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ከመጡ ህ.ወ.ሓ.ትን አድነዉ በሃገራችን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ያመጣሉ ነዉ እያልከን ያለሀዉ ? ይህም የዋህነት ይመስለኛል አሁንም 1ኛ የመንግስትን ያህል ሃብት የሰበሰቡ ናቸዉ ፤

ሁለተኛ እድሜም ገፍቷል፤ ሶስተኛ ተቀባይነት የለም፤፤ ስለሆነም እዚህ ላይም የስብሃት አባባል ውድቅ ነዉ።

እነዚህ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ህዝብ ዲሞክራሲ ልማት ፍትህ አጥቶ ከላይ እንደገለፅኩት ህዝቡ ተቸግሮ በአለም ተበታትኖ የከፋ ኑሮ ሲገፋ ስለህዝብ ችግር አጀንዳ አንስተዉ ሊነጋገሩስ ይቅርና ጭራሹም በዚህች አገር ምን ችግር እንዳለ ግምት ላይ አያስገቡም እንዳውም ከዚህ ድሃ ህዝብ የተወለዱ አይመስሉም፤፤ ከልዩ ፍጥረት የተፈጠሩ ነዉ የሚመስሉት ። እነዚህ በኔ እምነት በተለያዩ ጊዜ ከህ.ወ.ሓ.ት ተገንጥለውና በመተካካት የተቀነሱ በስልጣን ያሉ የህ.ወ.ሓ.ት መሪዎች ቢሰባሰቡ ህ.ወ.ሓ.ትን አክመዉ ለሞት ከመቃሰት አያድኑትም። ስብሃት ነጋ ያልተረዳዉ ነገር ቢኖር ህ.ወ.ሓ.ት የምትባል ፓርቲ አቶ ስብሃት ያለበት ፈራጅ ቡድን በ 1985 ዓ/ም የዲሞክራሲ ጥያቄ የሉአላዊነት ጥያቄ በማስነሳቱ በግፍ የታሰሩ የተባረሩ በዛ እንደወጡ የቀሩ እለት ነዉ ህ.ወ.ሓ.ት የሞተች መለስም አንተም በ1993 ዓ/ም ለነበረ የህ.ወ.ሓ.ት የሁለተኛ አንጃ መሰንጠቅ ለመምቻ ተብሎ ያመናችሁበት ነበር እሱም የ1985 ዓ/ም ታጋዩ ያስነሳዉ ጥያቄ ትክክል ነበረ ግን ምን ይሁን ኮለፍነዉብላችሃል።

« ስብሃት ነጋ አሁን ደግሞ የ ህ ወ.ዋ.ሓ.ት አባልና የትግራይ ህዝብ ታግሎ ያመጣውን ስርአት ማክበር ብቻ ሳይሆን ታግሎ ለመጣዉ ስርአት ቀዳሚ ግንባር በመሰለፍ ሊከብርና ሊያስከብር ሊያገኝ ሌሎችም እንዲያገኙ ማክበር አለበት» በገፅ 4 ሶስተኛ አምድ አንቀፅ ሁለት መስመር 25፤፤ አቶ ስብሃት የትግራይ ህዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያ ወገኖች ጋር ታግሎያመጣዉ ስርአት ነበር ግን በናንተ ተቀምቷል፤፤ አይቶ አጥቷል የትግራይ ህዝብ የደርግን ሁሉም አይነት ግፍ ያልፈራ በእናንተ ግን የመግስት ሰራተኛ ነጋዴዉ ፣ አርሶ ሰደሩ ፣ ወዛደሩ፣ ተማሪዉ ፈርቶ ተሸማቅቆ እንዲኖር ተርቦ እያለ አልራበኝም ታሞ እያለ አልታመምኩም ውሃ ጠምቶት አልጠማኝም እንዲል አድርጋችሁታል፤፤ ለባለስልጣን መውቀስ ሂስ ካደረገ ወደ ላይ አትንጠራራ ብሎ ጭንቅላቱን ደፍቶ እንዲሄድ ተደርጓል። ሌላዉ አቶ ስብሃት የትግራይ ህዝብ ታግሎ ያመጣውን ስርአት ፊት ተሰልፎ መጠበቅ አለበት ተብሏል፤፤ የማንና የማን ሃብት ህንፃ ሊጠበቅ ነዉ ይህ ማታለል ነዉ። የትግራይ ህዝብ በአሁኑ ጊዜ በወንዝ ተከልሎ ማሰብ ትቶ ተሻግሮ በሩቅ አይቶ የኢትዮጵያ አንድነትና ሉኣላዊነት ነዉ ሚታየዉ ያለዉ እምቢ ለጠባብነት እያለ ያለዉ።

የአቶ ስብሃት ጠባብ አመለካከት አልፏል ድሮም የህ.ወ.ሓ.ት አፈና ደርግን ለመጣል ሲባል ተሸፍኖበታል እንጂ ስለ አንድነት ጉዳይ ስለ ባህር በር ስለ ኤርትራ ጉዳይ ብዙ ጥያቄ አንስቶ እነ ስብሃት ምን አይነት መልስ ትሰጡት እንደነበራችሁ ራስህም ታውቀዋለህ። ስለዚህ የትግራይ ህዝብ ሃሳብህን አይቀበልህም።

ሌላዉ የትግራይ ህዝብ ይሁን መላዉ የኢትዮጵያ ህዝባችን የህ.ወ.ሓ.ት በ1983 ዓ/ም ደርግን አስወግዶ ወንበሩን ሲቆነጠጥ የህ.ወ.ሓ.ት መሪዎች ህዝቡ ታግሎ ባመጣዉ ድል ተጠቅማችሁ ከደርግ ተለይታችሁ ለመታየት ብዙ ዲሞክራሲ የሚመስሉ መግለጫዎች ትሰጡ ነበር።በመሬት ላይ የነበራችሁ ፖሊሲም ለምእራብ ሃገሮች ፖለቲካ ፍጆታ ብላችሁ ነፃ ኢኮኖሚነት መብት የምትጠብቁ ትመስሉ ነበር ቀስ በቀስ ግን የፀረ ዲሞክራሲ ባህሪያችሁ አገርሽቶበት እንደ ወትሮ ሆናችሁ የቻይና ታማኝነታችሁ አረጋግጣችሁ መሬት ለምን የህዝብ አላችሁ።

በአሁኑ ጊዜ የህ.ወ.ሓ.ት ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ መሪዎች የከተማም ሆነ የገጠር መሬት የኔ ነዉ 90 ሚሊዮን ህዝብ የመሬት ጢሰኛ ነህ ብላችሁ ፍፁም ዜግነቱ ቀምታችሁታል፤፤ ኢትዮጵያዊ ዜጋ መሆኑ እንዲጠራጠር አድርጋችሁታል፤፤ ታዲያ ስብሃት ነጋ የትግራይ ህዝብ የታገሉለት አላማ እንዳይቀማ ፊት ተሰልፎ ለህ.ወ.ሓ.ት ይጠብቃት ስትለን በ 17 አመቱ የትጥቅ ትግል የከፈለዉ ሂወትና ቁሳቁስ ያልጠቀመዉ አሁን እንደገና የህ.ወ.ሓ.ት መሪዎች ልጆቻቸዉ እንዲሁም ምንጩ የማይታወቅ የሰበሰቡት ሃብት ሊጠብቅ ነዉ የምትፈልገዉ? አይታሰብም ዋና ችግራችሁ ለሁሉም ስራችን መስተዋታችን ህዝብ ነዉ ስትሉ የነበረ በመክዳት በአሁኑ ጊዜ ህዝብ ምን ይላል የሚል መረጃ አለመኖራችሁ ነዉ እንጂ ህዝቡ ለውጥ ፈልጓል የህ.ወ.ሓ.ት መሪዎች ልክ ከባህር እንደወጣ አሳ ከልብ አውጥቶ ጥሏቹሃል። አሁን ግን ትልቁ ችግር ሆኖበት ያለዉ የመንግስት የፍትህ አካላት በደህንነት በፖሊስና ፌዴራል ፖሊስ በአቃቤ-ህግ ታፍኗል፤፤ በአሁኑ ጊዜ በሃገራችን ያለዉ አስተዳደርበአዋጅ ወታደራዊ አስተዳደር ስላልተባለ ነዉ እንጂ በተግባር ወታደራዊ አንባገነናዊ ስርአት ነዉ ያለዉ። ታዲያ ስብሃት ነጋ ለትግራይ ህዝብ ለዚህ ስርአት ጠብቀዉ ነዉ እያለ ያለዉ ደግሞ በባዶ ሆዱ እንዴት ብሎ ይታሰባል;

« የትግራይ ህዝብ ታግሎ የሚያታግለዉ የሚጠቅመዉ አብዮታዊ መሪ ድርጅት ያስፈልጋል›› ስብሃት ነጋ ገፅ 4 በአርእስት የተፃፈ» (በትግርኛ ህዝቢ ትግራይ ተቓሊሱ ዘቃልስ ዝጠቕሞ ወያናይ ውድብ ክረክብ ይግበኦ)

ስብሓት ነጋ እያልከን ያለሀዉ የትግራይ ህዝብ ታግሎ የሚያታግለዉ አብዮታዊ ፓርቲ ያስፈልገዋል ነዉ። በዚህ አባባል እኔም እስማማለሁ አዎን አብዮታዊ ፖለቲከዊ ድርጅት ያስፈልገዋል ።ግን የትኛዉ አብዮታዊ ፓርቲ; ህ.ወ.ሓ.ት ከማቃሰት እናድነዉ ከሆነ በትግራይ ክልል ህዝብ ይሁን ባጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ህ.ወ.ሓ.ት ኢ.ህ. ኣ.ዴ.ግን አይፈልግም፤፤ በወታደራዊ አስተዳደር ስለታፈነ በምርጫ ጊዜ ለፈለገዉ ቦታ የመረጠዉ ካርድ ስለተቀማ ከክልል እስከ ጎጥ በአንድ ለአምስት የደህንነት መዋቅር ስለታፈነ ብቻ ነዉ። ስለዚህ ከእንግዲህ የትግራይ ህዝብ ለስብሃትና ጓዶቹ ሎሌ ሆኖ አይኖርም፤፤ በሰላማዊ መንገድ ትግሉን በማስቀጠል የኢትዮጵያ ህዝብ የስልጣን ሉአላዊነቱ ሊያረጋግጥ ነዉ።

ግን አቶ ስብሀት ነጋ ሁሉ ግዘ ለትግራይ ህዝብ እየተቆረቆርክ መስለህ የጠባብንት አመለካከት ታሰራጫለህ፤፤

ይህንን ያልኩበት ምክንያት 90 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ህዝብ በአስከፊው የህ.ወ.ሀ.ት ኢ.ህ.አ.ደ.ግ መሪዎቹና ካድረዎቹ አፈና መዳፍ ገብቶ እያለ ለኢትዮጵያ ህዝብ እንደ ማሰብ ፋንታ የትግራይ ህዝብ ለብቻው ነጥለህ ለበሰበሰ ስርአታችሁ ዘበኛ ማድረግ አያዋጣም፤፤ የትግራይ ህዝብም አይቀበለውም፤፤ ለአንድነቱ የቆመ ነውና፤፤

‹‹ «ስብሃት ነጋ ሙስና ዋነኛዉ የስርአታችን አደጋ ነዉ›› ብሎ የተነሳ ፓርቲና መንግስት ለምን ወደዚህ የተበላሸ ሙስና አደጋ ደረሰ የሚል ጥያቄ በብቃትና በቆራጥነት ካለተፈታ በዚህች አገር ምን ሊፈጠር ነዉ? ሙስናና ብልሹነት ከቁጥጥር እየወጣ ነዉ የሚል ጥቆማ ከአገር ውስጥም ከውጭ አገር ለሚመለከተዉ ጥቆማዉ እንደ ጎርፍ ይፈስ ነበር በጊዜዉ ግን ሰሚ ጆሮ አላገኘም » ›› ውራይና መፅሄት ገፅ 3 አንቀፅ አንድ መስመር ሰባት፤፤

አቶ ስብሃት እንደምትለዉ ህ.ወ.ሃ.ት ከ1984 ዓ/ም ጀምሮ በስብሰባ በብዙሃን መገናኛ ስለሙስና ብዙ ይናገር ነበር፤፤ በተለይ ደግሞ የህ.ወ.ሃ.ት አመራሮች ሙስና በናንተ ነበር የተጀመረዉ፤፤ ምርጥ ቤት ለራስህ ለዘር መንዘርህ ለአንድ መሪ ከሁለት እስከ 3( 4 መኪና) መያዝ ነዳጅ ያለገደብ መጠቀም የራስህና የቤተሰብ ህን ኑሮ ማሻሻል ከውርሃዊ ገቢህ ጋር የማይመጣጠን በየቀኑና በየሳምንቱ በሂልተን በሶደሬ መዝናናት የቤት እቃዎች በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ወጭ ማድረግ ከባለሃብቶች ገፀ በረከት ስጦታ መቀበል፣ በየጊዜዉ ብዙ ወጭ በማውጣት ግብዣ ማድረግ ልዩ ፍጡር ሆነህ መታየት ረጅም ሳይጓዙ ወደ ይኩራሩበት የነበሩ የንጉሳዊ ቤተሰብ ቅምጥል ኑሮ እነሱን አልፈዉ ሄደዉ በየምሽቱ በአስር ሺህ ብር የሚቆጠር ገንዘብ ማባከን በልጅ ጥምቀት ፣ የልደት ቀን ሰንጋዎች ማረድ በዊስኪ መራጨት ጊዜ እየገፋ ሲሄድ በግልፅ የማይታወቅ ሃብት ማካበት በተለያየ መንገድ ሰማይ ጠቀስ ህንፃዎች መገንባትና ስም ቀይሮ ብዙ የደረቅና የፍሳሽ የጭነት መኪና መግዛት ሌላ ቀርቶ የመሪዎች ሚስቶች ውጭ አገር ሄደዉ እንዲወልዱና ለወደፊት በዛው የውጭ አገር ዜግነት ይዘዉ ቆይተዉ መሸሻ ቦታ ማዘጋጀት ብሎም ቤት መስራት ስልጣንህ ተጠቅመህ ዘርመንዘርህ ውጭ መላክ ነበር። ለዚሁ ማረጋገጫ በቻይና በ10 ሺህ የሚቆጠሩ የመሪዎች ልጆች የሚማሩ ኣሉ። ሌላ ዋነኛዉ በመንግስት ስራ አመዳደብ በሞያ እንደመሆን በዘመድ አዝማድ በጋብቻ በጓደኝነት አድርገህ ስራው በሞኖፖል መያዝ ሌላ ስራተኛ እንደ ሁለተኛ ዜጋ ማየት ነበር።

ኣቶ ስብሃት ይመሩት የነበረ የኢፈርት ድርጅቶች በአስር ቢሊዮን የሚቆጠር ካፒታል ያላቸውም ለስሙ በህዝብ ስም እየተነገደባቸው ለሙሰና ብልሹነት የተጋለጡ ሆነው የሄዱት ስፍር ቁጥር የላቸውም፤፤ ሁሉም ለስሙ በህዝብ ስም እየተነገደባቸዉ ለሙስናና ብልሹነት የተጋለጡ ሆነዉ የኦዲት ቁጥጥር የለባቸዉም፤፤ ሁሉም ገንዘቡን የሚያውቀዉ ስብሃት ነጋ ነበር፤፤ ቁልፉም እሱ ነበር ኃላም ስብሃት ሲለቅ ስዬ አብርሃ ቀጥሎ ኣባዲ ዘሞ በመጨረሻም አዜብ መስፍን የበላይ ጠባቂ ጠ/ሚኒስቴር መለስ ነበሩ።ስብሃት ነጋም እስከአሁን የግዙፍ ካምፓኒ የወጋገን ባንክ ቦርድ ዳይሬክተር ነህ፤፤ ይህ ባንክ ከፍተኛ አክሲዮን የህ.ወ.ሃ.ት ሃብት ነዉ ስንት ካፒታል አለዉ ማን ይቆጠቀጠረዉ የሚለዉ መልሱ ለስብሃት ነጋ ነዉ።

እንግዲህ የሙስና ጉዳይ ከተነሳ በዘመነ ህ.ወ.ሃ.ት ስርአት ሙስና በኢትዮጵያ አደጋዉ እንዲስተካከል አስተያየት የሚሰጡ ቅን አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የውጭ አንባሳደሮች መንግስታት የአለም ባንክም ምክር ይሰጡ ነበር፤፤ ለዚህ አስተያየት ከአቶ ስብሃት ጀምሮ ሁሉም የህ.ወ.ሃ.ት መሪዎች ሰሚ ጆሮ አይሰጡትም ነበር። ምክንያቱም ሁሉም የተነካኩ ናቸዉና። ስለዚህ ስብሃት ነጋ ‹‹የሙስና መረጃ እንደጎርፍ ይፈሱ ነበር ግን ሰሚ ጆሮ አልነበረም፤፤›› ስትለን አንተስ ሙስና ኣለ ብሎ መረጃ የሰጠህ ቅን ኢትዮጵያዊ እንደ ጠላት አይተህ ከስራ አላባረርክም ? በጥላቻ እንዲታይ አላደረክም ይህ አባባል ማታለያ ነዉ ። አንድ ነገር በዚሁ እድሜ በገፋበት በምፅተአለም ዋዜማ አገራችን በሰዉ ሃብት የሃገር ሃላፊነት የማይሰማቸዉ ጅቦችና ከወደመችና የአገራችን አንጡራ ሃብት ውጭ አገር ከሰፈረ በኃላ ሆነ ራሱ ግን የስብሃት ልግም እንጂ አብዮታዊ ነት አያሳይም።



ስብሃት ነጋ ‹‹የተበላሸ ሙሰኛ ሁሉ በየደረጃዉ መታረም አለበት ስርአቱን በመጣስ ቤት ከፍቶ የሰረቀ መሆኑ እያወቀና እየሰማ እርምጃ ያልወሰደ በከፍተኛ ደረጃ ጥፋት መጠበቅ አለበት። ያ ቤት ከፍቶ አግኝቶ ትንሽ የቀመሰ ደግሞ በሁለተኛ ደረጃ የሚስተካከል መሆኑ ህዝቡን ለማረጋጋት ያስችለዋል» ውራይና መፅሄት ገፅ 5 3ኛ አምድ አንቀፅ 3 መስመር አንድ

አቶ ስብሃት ነጋ አንደኛ ነገር አንተን ከሙስና ነፃ እንደሆንክ በሁለተኛ ደግሞ ቢሊየን የሰረቀና ሚሊዮን የሰረቀ እኩል መታየት የለባቸዉም፤፤ ምክንያቱም ትንሽ ለሰረቀ ቀላል ቅጣት ከሰጠኸዉ ህዝብ ሊረጋጋ ይችላል ብለሀናል። የትኛዉ ህዝን ነዉ? ግልፅ አይደለም፤፤ አሁን እኮ ዋና ሌባ የሚባለዉ ከቀበሌ እስከ ፌዴራል ያለዉ ባለስልጣን በሙስና ተራክሷል፤፤ ይህ መዋቅር ከህዝቡ ከ3 እስከ 5% ነዉ የሚሆነዉ ቅጣቱ ይቀላል ምትለዉ ያለህ ለማነዉ? ለምስ ነዉ የሚቀልበት? በኔ እምነት አቶ ስብሃት የምትለን ያለ ታች ሆኖ ህዝብ ያሰቃዩ ሎሌዎች ከተመቱ ለወደፊቱ በየመድረኩ እጅ እያወጣ የስ እያለ የሚውል ሰዉ አናገኝም፤፤ በምርጫ ጊዜ ኮረጆ የሚሰርቅ የለንም፤፤ ከሚል የመነጨ ነዉ ትንሽ የሰረቀ ይማር የምትለን ያለህ በሌላ በኩል ትልቁ ብልሹ ሙሰኛም ይመታ ስትለን ቁርጠኝነትህን አይደለም የሚያመለክት፤፤ አቶ ስብሃት ነጋ ትልቁ የሙስና ግንድ ከተመታ አንተም ልትመታ መሆንህ በመረዳትህ ነዉ የተድበሰበሰ ትንታኔ የተናገርከዉ። በኔ እምነት ግን በኢትዮጵያ ትልቁ ጠላት ሙስናና ብልሹ አስተዳደር ከግንዱ ብቻ ሳይሆን ከስሩ ከቀበሌ ጀምሮ መቆረጥ አለበት እላለሁ። እዚህ ላይ ግን የስብሃት አሰራር እማውቀዉ ነገር አለ፤፤ ስብሃት በስሙ ገንዘብ ይሁን ንብረት የለዉም። ብዙውን ጊዜም የሆነ ወጭ አይፈርምም ነበር፤፤ ሁሉም ነገር በውክልና ነበር የሚያሰራዉ ። ስለዚህ ትንሽ የሰረቀ ይማር ሲለንም እነዛ ወኪሎቹ እንዳይቆረጡ ካለዉ ስጋት ነዉ። የገንዘቡ ጎተራም ከነሱ ነዉ በስብሃት ወንድሞች ዘርመንዘሩ ስም የተሰሩ ህንፃዎች ምንጫቸዉ የማይታወቅ ሃብትም አላቸዉ።

ሌላዉ ስብሃት ነጋ ስለ ሙስና መረጃ ሲሰጥ ሰሚ ጆሮ አልነበርንም ብለህናል፤፤ ማነዉ የማይሰማ በግልፅነት ልትነግረን አትችልም ማነዉ ለሙስና ጨካኝ ያልሆነ ጠ/ሚኒስቴር? ውጭ ጉዳይ? መከላከያ ሚኒስቴር? የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ? ደረጃ መዳቢዎች? ያገር ውስጥ ገቢ ደህንነት? የከተማ ልማት? የአዲስ አበባ ከንቲባ ዳይሬክተር? እመቤትዋ የጥረት ዳይሬክተር? የወጋገን ዳይሬክተር? የመከላከያ ኢንጅነሪንግ ሚኒስትሮች? የክልል ውሃ ሃብት ኢንተርፕራይዝ ሃላፊዎች ? የስኳር ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር? የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ፓርቲዎች ናቸዉ ታዲያ አቶ ስብሃት ከፍተኛዉ ሙሰኛ ( ትልቁ) ቦታ ነዉ የሚገኘዉ ብለሃል፤፤ ከነዚህ የተኞቹ ናቸዉ ሙሰኞች፤፤ የአቶ ስብሃት አሽሙር አነጋገር 40 አመት ጊዜ ስለፈጀብህ በአንድ አረፍተ ነገር ይቅርና የማያውቅህ እኔም በአስር የሚቆጠሩ አመታት አብረን ተቀምጠን አሽሙርህ ሊረዳኝ አልቻለምና ለዚህ ትውልድ አሽሙር ከምናወርሰዉ ግልፅነትን እናውርሰዉ።

አቶ ስብሃት አንድ ጥያቄ ግን ልጠይቅህ በዚህ ፅሁፍ ላይ ያሰፈርከዉ ለትግራይ ህዝብ ብቻ ታግሎ የሚያታግለዉ መሪ ድርጅት ያስፈልገዋል ብለሃል በሌላ በኩል ደግሞ ህ.ወ.ሓ.ት እናድን ትላለህ እዚህ ላይ ሁለት ነገር እንድመለከት አድርጎኛል።

1ኛ ለትግራይ ህዝብ ብቻ ለምን አዲስ መሪ ድርጅት ያስፈልገዋል ? ተበላሽቶ ያለዉ የኢትዮያ ህዝብ መሪ ነኝ የሚለዉ ህ.ወ.ሓ.ት ኢ.ህ.ኣ.ዴ.ግ ክህመሙ ካላጋገመ ህ.ወ.ሓ.ት ብቻውን አክመህ ይድናል ወይ ? በሙሉ ተሟል ነውና ወይስ አዲስ የትግራይ መሪ ፓርቲ በመመስረት ወደ ዱሮ የነበርክበት አስተሳሰብ ነፃ ( ትግራይ ትግርኚ) የሰሜን ኢትዮጵያ መንግስት ለመመስረት አስበህ ይሆናል የሚል ጥርጣሬ አድሮብኛል፤፤ አባባልህ ለብዙ ዜጎች የተብራራ እይደለም፤፤ ደግሞ በቅርብ ጊዜ አሜሪካ ሄደህ ኤርትራዊ ነኝ ከማለትህ እጅጉን ተጠራጠርኩህ፤፤

2ኛ ለምን ህ.ወ.ሓ.ት ኢ.ህ.ኣ.ዴ.ግና አጋሮቹ እናድን ተበላሽተዋልና ብለህ በሃገር ደረጃ ላሉ ጓዶች ችግር ማየት ለምን ተሳነህ ? ወይ የህ.ወ.ሓ.ት መሪዎች ብቻ ነዉ የታመማችሁት ? አሁን ያለዉ ችግር እኮ የህ.ወ.ሓ.ት ኢ.ህ.ኣ.ዴ.ግ መሪዎች በሙስና መበላሸትና የመበስበስ አደጋ ነዉ አጋጥሟችሁ ያለዉ፤፤ አቶ ስብሃት በጥልቀትና በስፋት ብታስብበት፤፤ በአሁኑ ጊዜ ህ.ወ.ሓ.ት ብዙ ነገር ተበላሽቶባቸዋል፤፤ አንድ እርምጃ ለመራመድ ተስናችሁ በመቃሰት ላይ ናችሁ፤፤ በሰለጠኑ አገሮች እንደምናየው ከሆነ ይቅር እና እናንተ በስብሰባችሁ እንዳላችሁት ስብሰባዉ አንድ ቃል በውሸት ተናግረዉ ህዝብ ካወቃቸዉ ወይ ባገራቸዉ ከባድ ወንጀል ከተፈፀመ ከስልጣን ይወርዳሉ፤፤ እናንተ ግን አገር ያህል የባህር በር የሌላት አስቀርታችሁ የዘሂግ ፍርድ ቤት ውሳኔ ተሸንፋችሁ እያላችሁ አሸንፈናል ውሳኔዉ የኛ ነዉ ብላችሁ በመድረክ ዋሽታችሁ ይሀው ቁማችሁ ትሄዳላችሁ። በተጨማሪ የመላው ህዝብ ተቃውሞ እልባት ለማድረግ አልቻላችሁም፤፤ ይህም ከስልጣን ያወርዳል፤፤ እንደ ጃንሆይ ተጎትታችሁ ከወንበሩ ከምትወርዱ ለምን ይቅርብን ብትሉና ህዝብ የፈለገዉን መሪ ቢመርጥስ ?

ስብሃት ነጋ ከአሁን በኃላ የህ.ወ.ሓ.ት መሪዎች ከህመማችሁ አገግማችሁ ህ.ወ.ሓ.ት እናድናት ማለትህ የዋህነት ነዉ። ዋና ችግርህ የህዝብን ፍጎትና ልብ ትርታ ኣለመረዳትህና የትግራይ ክልል ህዝብ ከህ.ወ.ሓ.ት መሪዎች የተፋታ መሆኑን አልደረስክበትም፤፤ በሸራተን ሆነህ ስለ የትግራይ ህዝብ ከመናገር እስቲ ወደ ገጠር ህ/ሰብ ስሜቱን አጥና ። እናንተ ህዝቡን ለማደናገር ብላችሁ የምትናገሩትና የምትሰሩት አበጥሮ ያውቃልና።
አስገደ ገብረስላሴ ከመቀሌ


No comments:

Post a Comment