Tuesday, July 16, 2013

በቂልንጦ እስርቤት የእሰረኞች ደም በድብደባ እንደጎርፍ መፍሰሱን የአይን እማኞች ተናገሩ

በቂልንጦ እስርቤት የእሰረኞች ደም በድብደባ እንደጎርፍ መፍሰሱን የአይን እማኞች ተናገሩ





አርብ ፣ ሀምሌ 6 2005 ዓም በእነ አቶ ተሻለ ኮርኔ መዝገብ የተከሰሱ 69 የኦሮሞ ተወላጆች ፍርድ ቤት መቅረብ ሲገባቸው፣ ፍርድ ቤት የሚወስዳቸው ፖሊስ ያጣሉ። በቅጽል ስሙ ሻእቢያ እየተባለ የሚጠራውን የእስር ቤቱን ሀላፊ ሲጠይቁት ቀጠሮአቸው ለ4 ወር መራዘሙን ይነግራቸዋል። እስረኞቹም ” ከ2 አመታት በላይ የላፍትህ ታስረን በመጨረሻ ብይን በሚሰጥበት ወቅት ለ4 ወራት ተራዝሟል መባሉ ተገቢ አይደለም” በማለት ለጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ የሚላክ ፊርማ ማሰባሰብ ሲጀምሩ ማረሚያ ቤቱ መረጃው ይደርሰውና 69ኙ እሰረኞች በ20 ተከፋፍለው ወደ ተለያዩ የማረሚያ ክፍሎች ወይም ዞኖች እንዲበተኑ ይደረጋል።
አርብ ጧት ሌሎች እስረኞች ወደ ውጭ እንዳይወጡ ከተደረገ በሁዋላ ፣ ሻእቢያ በሚባለው የእስር ቤቱ ሀላፊና ከውጭ በመጡ የፌደራል ፖሊስ አባላት እንዲደበደቡ ይደረጋል። አስተባባሪ ናቸው የተባሉትን 18 እስረኞችን እንደገና በማውጣት በሰደፍና እና በዱላ ከቀጠቀጡዋቸው በሁዋላ 8ቱ ራሳቸውን ሲስቱ ወደ እስር ቤቱ የህክምና ክፍል ይወሰዳሉ። ችግሩ ከአቅሙ በላይ መሆኑን የእስር ቤቱ የህክም ክፍል በመግለጹ፣ በአምቡላንስ ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል።
የአይን እማኞች ለኢሳት እንደገለጹት እስረኞቹ የተደበደቡበት ቦታ በደም በመጨቅየቱ አርብ እለት በውሀ ሲታጠብ አርፍዷል።
ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል በላይ ኮርሜ ፣ ተፈሪ ቀብኔሳ እና መንግስቱ ግርማ የሚባሉ ይገኙበታል።
በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የአህኮ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና እሰረኞቹ መደብደባቸውንና የተወሰኑት ሆስፒታል መግባታቸውን መረጃው እንደደረሳቸው ገልጸዋል።
ዶ/ር መረራ “ድርጊቱን በተደጋጋሚ ለመንግስት አመልክተን መልስ በማጣታችን መንግስት ሆን ብሎ በፖሊሲ ደረጃ ይዞ የሚያካሄድ ይመስላል” ሲል አክለዋል።
የእስር ቤቱን ሀላፊዎች ለማግኘት ሙከራ ብናደርግም አልተሳካልንም።

ኢሳት ዜና

No comments:

Post a Comment