Saturday, October 11, 2014

እስር ቤት ውስጥ የሚገኙት ኢትዮጵያውያን መልዕክት!!!

  አቶ በቀለ ገርባን፣ አቶ ኦልባና ሌሊሳን፣ አዛውንቱን ሲሳይ ብርሌን፣ አቶ ጉታ ዋቆንና ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬን አግኝተዋል፡፡ 
‹‹ህብረ ብሄር ፓርቲዎች ተጠናክረው የብሄር ፓርቲዎችን ማጥፋት አለባቸው›› አቶ በቀለ ገርባ
ከዝዋይ ወደ ቃሊቲ ከመጣሁ 11 ወራት ሆኖኛል፡፡ በህዳር ወር 2006 ዓ.ም ነው ወደ ቃሊቲ የመጣሁት፡፡ በአሞክሮዬ መሰረት ጥር 11 ቀን 2006 ዓ.ም መፈታት ቢገባኝም አሁንም ድረስ እስር ቤት ውስጥ እገኛለሁ፡፡ በወቅቱ በአሞክሮዬ መሰረት መፈታት እንዳለብኝ ለእስር ቤቱ ኃላፊዎች ደብዳቤ ጽፌ ነበር፡፡ ሊፉቱ ሲፈልጉ አስጠርተው ያነጋግሩሃል፡፡ ካልፈለጉ ደግሞ ዝም ይሉሃል፡፡ እኔ ደብዳቤ ብጽፍም አልተጠራሁም፡፡ ምክንያታቸውን ባላውቅም ሊፈቱኝ አልፈለጉም ማለት ነው፡፡ ግን በአሞክሮዬ ባለመፈታቴ አልተጎዳሁም፡፡ በርካታ ነገሮችን ተምሬበታለሁ፡፡ እንዲያውም የሚጎዱት እነሱው ራሳቸው ናቸው፡፡ በርካታ ታሳሪዎች አሳሪዎቹ ለቃላቸውም ሆነ በህጉ ተገዥ እንዳልሆኑ በእኔ ጉዳይ ተምረዋል፡፡ አሁን በመጋቢት ወር ዋናውን ፍርድ ጨርሼ እፈታለሁ ብዬ እጠብቃለሁ፡፡
እኔ የማምነው በባለሙያነቴ ነው፡፡ ፖለቲከኛ ነኝ ብዬ አላምንም፡፡ እንደዛም ሆኖ ግን እንደ ግለሰብ ፍትህን እሻለሁ፡፡ ስልጣን ላይ ማንም ይምጣ ማን ፍትህን የሚሰጥ ከሆነ ችግር የለብኝም፡፡ በሙያተኝነቴ ነው መቀጠል የምፈልገው፡፡ ነገር ግን ክፍቶች አሉ፡፡ ወደ ፖለቲካው የገባሁትም ክፍተቶችን በማየቴ ነው፡፡
ህብረ ብሄራዊ የሚባሉ ፓርቲዎች ለአብዛኛው ህዝብ ተደራሽ አይደሉም፡፡ የህብረ ብሄር ፓርቲዎች ድክመት ደግሞ የብሄር ፓርቲዎች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል፡፡ በእነሱ መዳከም ነው የብሄር ፓርቲዎች በየ ቦታው ለመመስረት እድል የሚያገኙት፡፡ ህብረ ብሄር ፓርቲዎች የአንድን ማህበረሰብ ችግር ለመፍታት አቅም የላቸውም ብሎ ያሰበ አካል/ሰው እወክለዋለሁ በሚለው ማህበረሰብ ስም ፓርቲ ያቋቁማል፡፡ እኔም በዚህ ክፍተት ነው ወደ ፖለቲካው የገባሁት፡፡ ይህ ችግር ባይኖር ማህበረሰብን ከፋፍሎ ‹‹ይህኛው ፓርቲ የዚህ፣ ያንኛው ደግሞ የዚህኛው ማህበረሰብ ፓርቲ ነው›› ተብሎ እንዲከፋፈል ፍላጎት የለኝም፡፡
ህብረ ብሄራዊ ፓርቲዎች ቢጠናከሩ በአንድነት መታገልን የመሰለ ነገር የለም፡፡ ከአንዱ ዓለም አራጌ ጋር በታሰርንበት ወቅት ‹‹እናንተ ከተጠናከራችሁ እኛ እንጠፋለን፡፡ እናንተ ተጠናክራችሁ በብሄር የተደራጀነውን ማጥፋት አለባችሁ፡፡ ተጠናከሩና እኛን አጥፉን፡፡ ያኔ ሁላችንም በአንድነት እንታገላለን፡፡ ችግሮችም ይፈታሉ›› እለው ነበር፡፡ የህብረ ብሄራዊ ፓርቲዎች አለመጠናከር እንጅ ለዚህኛው አሊያም ለዛኛው ህዝብ ብዬ መስራት አልፈልግም፡፡ በአንድነት መስራትን የመሰለ ነገር የለም፡፡
ህብረ ብሄር ፓርቲዎች በአንድ በኩል በመረጃ እጥረት፣ በሌላ በኩል በስህተት፣ አሊያም አይቶ በማለፍ የአንድን ማህበረሰብ ችግር ችላ ይሉታል፡፡ ይህ ነው ተነጣጥሎ ለመታገል፣ ለብሄር ፓርቲዎች መበራከት ምክንያት የሆነው፡፡ ህዝብ መብቱ እስከተከበረለት ድረስ ማን መጣ ማን ትኩረት አይሰጥም፡፡ ህብረ ብሄር ፓርቲዎች መዳከም ግን የብሄር ፓርቲዎች ተደማጭነት እንዲያገኙ ምክንያት ሆኗል፡፡ አሜሪካን ለምሳሌ ብንወስድ ህዝቡ መብቱ እስከተከበረለት ድረስ ጥቁር መራ ነጭ ችግር የለበትም፡፡ የእኛ አገርም ጉዳይ ተመሳሳይ መሆን ይችላል፡፡ በዚህ ላይ እኛ ወንድማማቾች ነኝ፡፡
እኔ ህብረ ብሄር ፓርቲዎችን እወቅሳለሁ፡፡ እነሱ ከተጠናከሩ በየቦታው በተናጠል የሚደረገው ትግል ወደ አንድ ጠንካራ ትግል ይመጣል፡፡ እነሱ ከተጠናከሩ በተናጠል የሚደረገው ጭቆና ይቀንሳል፡፡ ክፍተት ባይኖርና ህብረ ብሄር ፓርቲዎች ለሁሉም ህዝብ መድረስ ቢችሉ እኔ በሙያዬ በቀጠልኩ ነበር፡፡ እንዲህ የምንታሰረውም እኩ ከድክመታችን የተነሳ ነው፡፡ ጠንካራ ህብረ ብሄራዊ ፓርቲ ቢኖረን እኮ እኛም አንተሰርም ነበር፡፡ ይህ ካልሆነ ግን የአገራችንን ችግር መፍታት አንችልም፡፡ በተናጠል ለጭቆና እንዳረጋለን፡፡ በተናጠል እንታሰራለን፡፡ በሂደት ጭቆናውን እየለመድነው እንሄዳለን፡፡ በዚህ ሁኔታ ለውጥ ማምጣት አንችልም፡፡
‹‹ኢትዮጵያ ጭንቅ ላይ እንዳለች እርጉዝ ሴት ነች›› አቶ ሲሳይ ብርሌ
የተፈረደብኝ 13 አመት ነው፡፡ ከታሰርኩ አራት አመት ሆኖኗል፡፡ እድሜየ 65 ደርሷል፡፡ እስር ቤት ውስጥ ችግር አለ፡፡ የእስር ቤቱን ኃላፊዎች የምናገኛቸው ህክምና ስንፈልግ ነው፡፡ ነገር ግን የህክምናው ጉዳይ ባይወራ ይሻላል፡፡ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ በእርግጥ ውጭ ያለው ህዝብም በሰፊው እስር ቤት ውስጥ እንዳለ ነው የሚቆጠረው፡፡ ልዩነቱ የተሻለ ነፋስ ስለምታገኙ፣ ስለምትዘዋወሩና የፈለጋችሁትን ሰውም ስለምታገኙ ነው፡፡
እኛ እያረጀን ነው፡፡ ከእድሜያችን አንጻር በትግሉ ሂደት ብዙም የምንጨምረው ነገር ላይኖር ይችላል፡፡ እናንተ ወጣቶች ናችሁ፡፡ ለትግሉ መሰረት የምትጥሉበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ ወጣትነት ለትግል ወሳኝ ጊዜ ነው፡፡ አባት ያላወረሰውን ልጅ ሊያስቀጥል አይችልም፡፡ እናንተ አሁን ለራሳችሁ ብቻ ሳይሆን ለልጆቻችሁም ጭምር ነው የምትታገሉት፡፡ እናንተ በርትታችሁ ካልታገላችሁ ልጆቻችሁ ምንም የሚወርሱት ነገር አይኖርም፡፡ አባት ያላወረሰውን ደግሞ ልጅ ምንም ነገር ሊያስቀጥል አይችልም፡፡ በመሆኑም እናንተ ከአሁኑ ለእውነት በመቆም ልጆቻችሁ የሚያስቀጥሉት ነገር መስራት አለባችሁ፡፡
ጭቆና እስካለ ድረስ እኔም ሆንኩ እናንተ ባንታገልም ጭቆናውን ለማስወገድ የሚነሳ ሰው አይጠፋም፡፡ እናንተን እድለኛ የሚያደርጋችሁ ጭቆናውን ለመግታት ፈልጋችሁ፣ በራሳችሁ ተነሳሸነት በመጀመራችሁ ነው፡፡
ጭንቅ ላይ ያለች እርጉዝ ሴት ካላማጠች አትገላገልም፡፡ ለእኔ ኢትዮጵያ ጭንቅ ላይ እንዳለች እርጉዝ ሴት ነች፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ከሚደርስባት ስቃይ ለመገላገል ማማጥ አለባት፡፡ ያኔ ትገላገለዋለች፡፡ ለዚህ ደግሞ ትግል ያስፈልጋል፡፡ ወጣቶች መታገል አለባችሁ፡፡ ትግሉ ጥንካሬን ይጠይቃል፡፡ መጠንከር አለባችሁ፡፡
‹‹ተቃዋሚዎች በምርጫው ካላመኑበት ሁላችንም አንገባም ማለት አለባቸው›› አቶ ኦልባና ሌሊሳ
የፖለቲካ ፓርቲዎች ስለ ምርጫው ቀድመው መስራት አለባቸው፡፡ ምርጫ ስለመግባት አለመግባት ከመወሰናቸው በፊት ጠንክረው መስራት ይገባቸዋል፡፡ ውሳኔውን ከመወሰናቸው በፊት ውሳኔውን ተከትሎ ሊመጣ የሚችለውን ነገር ማሰብ አለባቸው፡፡ ይህ ጉዳይ ጥናት ያስፈልገዋል፡፡ ለውሳኔያቸው ደግሞ ተገዥዎች መሆን አለባቸው፡፡ አንዴ ከተወሰነ በኋላ ጠንካራ አቋም መያዝ አለበት፡፡ በህዝቡ አመኔታ ለማግኘት በውሳኔያቸው መጽናት አለባቸው፡፡ መወላወል አይገባም፡፡ ጊዜው እስኪደርስ ጠንክረው መስራት አለባቸው፡፡ በአንድ ወቅት 33 የሚባል ስብስብ ነበር፡፡ አሁንም ተባብሮ መስራት ያስፈልጋል፡፡ ለምርጫው በጋራ መስራት ያስፈልጋል፡፡
ተቃዋሚዎች በምርጫው መሳተፍ ለህዝብ የማይጠቅም መሆኑን ካመኑ እና መግባት የማያስፈልጋቸው ከሆነ በአንድነት ኃይልን አሰባስቦ ከምርጫው መውጣት ይቻላል፡፡ በምርጫው ካላመኑበት ሁላችንም አንገባም ነው ማለት ያለባቸው፡፡ በተናጠል ከምርጫው ራስን ማግለል ጥቅም አይኖረውም፡፡ በእርግጥ ይህ መወሰን ያለበት ጊዜው ሲደርስ ነው፡፡ እስከዛ ግን ጠንክረው መስራት አለባቸው፡፡
መጥታችሁ ስለጠየቃችሁን በጣም እናመሰግናለን፡፡ ውጭ ያለውን የቤት ስራችሁንም ጠንክራችሁ መስራት አለባችሁ፡፡
ነገረ ኢትዮጵያ በቀጣይ ጊዜያትም እስር ቤት ውስጥ የሚገኙትን ሌሎች ኢትዮጵያውያን መልዕክት ለማቅረብ ትጥራለች፡፡

No comments:

Post a Comment