Thursday, May 9, 2013

ሰማያዊ ፓርቲ የአፍሪካ ኅብረት 50ኛ ዓመት በዓል ሲከበር ሰላማዊ ሠልፍ ለመጥራት መወሰኑን አስታወቀ


በኢትዮጵያ የሚፈጸሙ የተለያዩ የሰብዓዊ፣ ዴሞክራሲያዊ መብት ጥሰቶችና ሕገወጥ ድርጊቶች እንዲቆሙ ለመንግሥት በተለያዩ 
ጊዜያት ጥያቄዎችን ቢያቀርብም፣ ከመንግሥት በኩል ምንም ምላሽ ማግኘት ባለመቻሉ የአፍሪካ ኅብረት 50ኛ ዓመት በዓል በሚከበርበት ወቅት፣ ጥቁር ልብስ በመልበስ ሰላማዊ ሠልፍ ለማድረግ መወሰኑን ሰማያዊ ፓርቲ አስታወቀ፡፡ 





ማክሰኞ ማለዳ በጽሕፈት ቤቱ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጠው ሰማያዊ ፓርቲ፣ ግንቦት 17 ቀን 2005 ዓ.ም. በሚከበረው የአፍሪካ ኅብረት 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓልና በዓሉ ከሚከበርበት ሁለት ቀናት ቀደም ብሎ ከግንቦት 15 ቀን ጀምሮ ሕዝቡ ጥቁር ልብስ እንዲለብስ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡ “የአሜሪካ ፕሬዚዳንትን ጨምሮ ሁሉም የአፍሪካ መሪዎች፣ የሌሎች አገሮች መንግሥታትና ተፅዕኖ ፈጣሪዎች በሚገኙበትና በሚሰበሰቡበት የአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ ፊት ለፊት ግንቦት 17 ቀን 2005 ዓ.ም. ሰላማዊ ሠልፍ በማድረግ ድምፃችንን እናሰማለን፤” ያሉት የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበርና የምርጫ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ስለሺ በይሳ ናቸው፡፡ 
ኃላፊው እንዳብራሩት፣ ለፍትሕና ለዴሞክራሲ ሥርዓት መስፈን የሚታገሉ ጋዜጠኞች፣ የፓለቲካ ፓርቲዎችና አባላትን በአሸባሪነት ስም ማሰቃየትን ፓርቲው ይቃወማል፡፡ መንግሥት የታሰሩትን እንዲፈታም ጠይቋል፡፡ ዜጎች ሕገ መንግሥታዊ መብቶቻቸው ተጥሷል፡፡ ከኖሩበት ቦታ በታጠቁ ኃይሎች እንዲፈናቀሉ ማድረግ የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው፡፡ በመሆኑም ድርጊቱን የፈጸሙ ለፍርድ መቅረብ እንዳለባቸው ፓርቲው ሌላ ጥያቄ አቅርቧል፡፡ 
መንግሥት በሃይማኖታችን ጣልቃ አይግባ ብለው የጠየቁ የእስልምና ዕምነት ተከታዮች ታስረዋል፡፡ በአሸባሪነት ወንጀልም ተከሰዋል፡፡ በእስር እንዲማቅቁና ሰብዓዊ መብታቸው እንዲጣስ መደረጉ እንዲቆም ፓርቲው መጠየቁን፣ መንግሥት የኑሮ ውድነትን፣ ሥራ አጥነትንና በሙስና የተዘፈቁ ሹማምንትን ፖሊሲ በማውጣት እንዲቆጣጠር ቢጠየቅም፣ ጥያቄዎቹን ከማንቋሸሽ፣ ከማጣጣልና ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ ከማለፍ ውጪ ምንም ምላሽ አለመስጠቱን ገልጸዋል፡፡ 
በመሆኑም ሰማያዊ ፓርቲ የመግለጫ ፓርቲ ብቻ ሳይሆን፣ ሰላማዊ ትግል የሚፈቅደውንና በሕገ መንግሥቱ የተፈቀደውን ለማድረግ ጠንክሮ እየሠራ መሆኑን አቶ ስለሺ ተናግረዋል፡፡ 
ፓርቲው በጥሩ እንቅስቃሴ ላይ መሆኑን፣ የሚቻለውን ሁሉ እያደረገና በሕዝብ ዘንድም ተቀባይነቱ እየጨመረ መምጣቱን የሚናገሩት ምክትል ሊቀመንበሩ፣ ከነባር ፓርቲዎች ባልተናነሰ እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ 
ፓርቲው በሐዋሳ፣ በምሥራቅ ጐጃም፣በ ሸካ፣ በጐንደርና በድሬዳዋ የዞን አስተባባሪዎች እንዳሉት የገለጹት አቶ ስለሺ፣ ከገንዘብ ጀምሮ ብዙ ችግሮች ቢኖርባቸውም፣ በአባሎቻቸው ላይ እየደረሰ ያለውን ተፅዕኖ በመቋቋም ጠንክረው እየሠሩ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ 
ከፍተኛ አመራሩም ሆነ የምክር ቤቱ አባላት እንደሚተማመኑና ከልባቸው እየታገሉ መሆኑን የገለጹት አቶ ስለሺ፣ አንዳንዶቹ በሌላ ፓርቲ ውስጥ የነበሩና አለመተማመን ያመጣው ጣጣ ሰለባ የነበሩ ስለሆኑ በደንብ እንደሚተዋወቁ በመግለጽ፣ እርስ በርሳቸው አንዱ አንዱን በመሰለል ለገዢው ፓርቲ መረጃ ያቀብላል ለሚለው አሉታ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ 
በሰማያዊ ፓርቲ ውስጥ ሆነው ለገዢው ፓርቲ መረጃ የሚያቀብሉ እንዳሉና አልፎ አልፎም ተለጣፊ ፓርቲ እንደሆነ ስለሚነገረው ጉዳይ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ስለሺ፣ “እዚህ አገር ተሰባስበህ ስትሠራ ስም ይሰጥሃል፡፡ ከቅንጅትና ከአንድነት ጋር ቢያያይዙን እውነት ነው፡፡ ከኢሕአዴግ ጋር ግን እንኳ በፖለቲካ ደረጃ የሥራም ግንኙነት የነበረው አባል የለንም፤” ብለዋል፡፡ 
የፓርቲ አባላት የፖለቲካ እንቅስቃሴ ገብቷቸው ሳይሆን የጥገኝነት መጠየቂያ ሰነድ ለማግኘት አባል እንደሚሆኑ፣ ለዚህም ማረጋገጫ በቅርቡ በአመራር ደረጃ የነበረ አባል መሰደዱን በሚመለከት ማብራሪያ የሰጡት አቶ ስለሺ፣ ‹‹አይኖርም ማለት አይቻልም›› ካሉ በኋላ፣ በቅርቡ ተሰዷል ስለተባለው አባላቸው ደግሞ ‹‹አባሉ ጌታቸው አርዓያ ይባላል፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ መሥራችና ስሙንም የሰየመው እሱ ነበር፡፡ የሥራ አስፈጻሚና የምክር ቤት አባልም ነበር፡፡ ከሰባት ወራት በፊት ግን ማመልከቻ በማቅረብ ከአመራርነት ወርዶ በተራ አባልነት ቀጥሎ ነበር፤” ብለው፣ የፓርቲው አባል ከመሆኑ በተጨማሪ ፍትሕ ጋዜጣ ላይ ይሠራ ስለነበር ደኅንነቶች እየተከታተሉት እንደተቸገረ እንደነገራቸውና በኋላም ተሰዷል መባሉን እንደሰሙ ተናግረዋል፡፡ 

No comments:

Post a Comment