>>>የሰው ህይወት ከዱር እንሰሳ ያነሰበት!
ከነዚህ ስደተኞች አብዛኞቻችን በፖለቲካ ችግር ሳቢያ የሚወዷትን ኣገራቸውን ለቀው የወጡ ናቸው። የተቀሩትም ባገራቸው ሰርተው የመለወጥና ራሳቸውን ችለው ቤተሰቦቻቸውን የመደገፍ እድል ተነፍገው በፖለቲካ ኣመለከከታቸዉ አነ በዘረቸው ምከነያት በደረሰበቸው ግፉ ርቀው የሄዱ ናቸው። ባገራቸው ነግደው፣ ኣርሰው፣ ኣርብተው ኣልያም ባላቸው ሞያ ኣገልግለው እንዳይለወጡ ስልጣን ላይ ያለው ስርኣት እንቅፋት ሆነባቸው። የወያኔ መንግስት ባገራቸው ከማናቸውም መንግስታዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ነጻ ሆነው ሰርተው መሻሻል የሚፈልጉትን ዜጎች የግድ የፓርቲዬ ኣባል ካልሆናችሁ እያለ ያስፈራራቸዋል። ይህን የማይቀበሉትን በሰበብ ኣስባቡ ኣደናቅፎ የስራ እድል ይዘጋባቸዋል። ኣርሶ ኣደሮቹን የማዳበሪያና የምርጥ ዘር ዋጋ ያስወድድባቸዋል ኣልያም ከናካቴው ይከለክላቸዋል። ነጋዴዎቹን ውሃ ቀጠነ ብሎ በማስቸገር የንግድ ፈቃዳቸውን ከነጠቀ በሁዋላ ይህን ያህል ሺ ገንዘብ ካልከፈልክ ኣታገኝም ይላቸዋል። ወደ ንግዱ ኣለም ለመግባት ያላቸውን ሃብት ኣስይዘው ከባንክ ገንዘብ መበደር የሚፈልጉትን በቅድሚያ የፓርቲያችን ኣባልነት መታወቂያ ኣምጣ በማለት ያሰናክላቸዋል። እነዚህ እንቅፋቶች ዜጎች ባገራቸው ሰርተው ራሳቸውንም ሆነ ኣገራቸውን እንዳያሳድጉ በማደናቀፍ ልባቸው ስደት እንዲመኝ ገፋፉ። ከኢትዮጵያ እየወጡ ወደተለያዩ ኣገራት ስራ ፍለጋ የተሰደዱ ዜጎች ቁጥር ከማናቸውም የጎሮቤቶቻችን ኣገሮች ልቆ የሚገኝበት ምክንያትም በዚህ ኣይነቱ የመንግስት ተጽእኖ ሳቢያ ነው ቢባል ማጋነን ኣይሆንም።
እነዚህ ስራ ፍለጋ የሚንከራተቱ ዜጎች የኢትዮጵያ ዜጎች እስከተባሉ ድረስ በደረሱበት ሁሉ ደህንነታቸውን የመከታተል ሃላፊነት የወደቀው ኣገር መሪ ነኝ በሚለው የወያኔ መንግስት ጫንቃ ላይ ነው። የወያኔ ህወሃት መንግስት ግን በኣንጻሩ ስደተኞቹ በደረሱባቸው ኣገራት ለሰብኣዊ ፍጡር የማይገቡ የጭካኔ እርምጃዎች ሰለባ እንዲሆኑ በማድረጉ ሴራ ውስጥ በቀጥታም ባይሆን በተዘዋዋሪ ተሳታፊ መሆንን መረጠ። በተለያዩ ጊዜያት ዜጎች ለስራ ፍላጋ በተሰደዱባቸው ኣገራት ተገድለው ሬሳቸው ጎዳና ላይ ሲጣል፣ ደማቸው እንደ ውሻ ደም የትም ሲፈስ ወያኔ ይህ ለምን ሆነ ብሎ ሲጠይቅ ኣልተሰማም።
ሰርተው ለመቀየር ያለሙ የኣገራችን ሴቶች ለግርድና ስራ ወደ ኣረብ ኣገራት ተሰድደው በጭካኔ ሲገደሉ፣ ሲደፈሩና ያፈሩትን ጥሪት ሲነጠቁ በተደጋጋሚ ተሰምቷል። ኣንዳንዶቹ ምሬት ጠንቶባቸው ከፎቅ ላይ ራሳቸውን ወርዉረው ነፍሳቸውን እንዳጠፉም ይታወቃል። ከኣንድ ኣመት ገደማ በፊት ኣለም ደቻሳ የተባለች የኦሮሞ ተወላጅ በቤይሩት ጎዳና ላይ በኣገሬው ሰዎች እንደ እባብ ስትቀጠቀጥ የሚያሳይ ቪድዮ በ ዮቲዩብ መለቀቁ ይታወሳል። ኣለም በወቅቱ እነዚያ ኣረመኔ የኣረብ ወጣቶች የሴትነት ክብሯን ደፍረው እርቃኗን ጎዳና ለጎዳና እየጎተቱ ሲጫወቱባት እዚያ ኣገር የሚገኘው የወያኔ ኤምባሲ እንዲደርስላት እያለቀሰች ስትማፀን በዚያው ቪድዮ ላይ ተስምታለች። ኤምባሲው ግን ኣልደረሰላትም። የሚገርመው ደግሞ ኣለም ደቻሳ ላይ እንዲህ ያለው ዘግናኝ በደል የደረሰው የወያኔ ኤምባሲ ካለበት ሁለት መቶ ሜትሮች ብቻ ርቆ በሚገኝ ስፍራ ላይ መሆኑ ነው። የወያኔ መንግስት በዚህ ኣንገብጋቢ ጉዳይ ላይ የኣገሪቷን መንግስት የጠየቀው ነገር ኣልተሰማም።
በቅርቡም እንደሚታወቀው ሳዉዲ ኣረቢያ ውስጥ በስራ ላይ ተሰማርተው ይኖሩ በነበሩ የኢትዮጵያ ዜጎች ላይ ኣስነዋሪ የጭካኔ እርምጃዎች ለሳምንታት ሳይቁዋረጡ እየተወሰዱ ናቸው። በዚህም እርምጃ ቢያንስ የሶስት ዜጎች ህይወት ጠፍቷል። የሳውዲ ፖሊሶች ከኣገሬው ወጣቶች ጋር በመሆን ዜግነታቸው ከኢትዮጵያ በሆነ ስድተኞች ላይ የተለየ ኣስነዋሪ የጭካኔ ድርጊት ሲፈጽሙ በተቀረጸው የቪድዮ ምስል ታይተዋል። ይህ ሁሉ ሲሆን እነዚህ የሚደበደቡ፣ የሚገደሉና የሚደፈሩ ዜጎች የትውልድ ኣገር መንግስት የሆነው ወያኔ ኣፉን ሞልቶ ድርጊቱን ሲያወግዝ ኣልተሰማም።
እንደ ኢንዶኔዢያና ፊሊፒንስ ያሉ መንግስታት ዜጎቻቸው ከሳውዲ በሃይል መፈናቀላቸውን ተቃውመው ወዲያውኑ የቅሬታ መግለጫ በማውጣት የሳውዲን መንግስት ኣወገዙ። በሳውዲ የሚኖሩትን የሃገራቸው ስደተኛ ዜጎች ደህንነት ለማስጠበቅ ባላቸው ኣቅም ሁሉ እርምጃ ወሰዱ። የወያኔ መንግስት ግን እንዲህ ያለውን መንግስታዊ ሃላፊነት መወጣት ቀርቶ እንዲያውም የሳውዲን መንግስት ጸረ ሰብኣዊ መብት እርምጃ ለመደገፍ እየተሞዳሞደ መሆኑን በራሱ ላይ መስከረ። በኣገሩ ዜጎች ላይ ሳውዲ ውስጥ እየደረሰ ላለውና ኣለምን እያሳዘነ ለሚገኘው ውርደት ስሜት ኣልነበረውም። ወያኔ ዘንድ ዋጋ የሚያወጣው ለኣገሩ ዜጎች ክብር መቆም ሳይሆን ለሳውዲ ኢንቨስተሮች መሬት ሸጦ ኣልያም በነጻ ሸንሽኖ እየሰጣቸው በኣጸፋው በሚወረወርለት ጥቅማ ጥቅም የንዋይ ጥማቱን ማርካት ብቻ ነው። ዜጎች ኣገራቸው ላይ ሰርተው እንዳያድጉ በሰበብ ኣስባቡ ገፍቶ በማስወጣት እነርሱ ለቀው የሄዱለትን መሬት ዛሬ ዜጎቹን እየገደሉ ላሉት የኣረብ ጥጋበኞች ይቸበችባል። ይህ የኣንድ ጸረ ህዝብ መንግስት ትልቁ መለያ ምልክት ነው።
እንደ ሱዳን፣ የመን፣ ጅቡቲ፣ ሶማሊ ላንድ፣ ፑንት ላንድ፣ ኬንያና በመሳሰሉት ሃገራት ውስጥ ከረጅም ጊዜ በፊት ጀምሮ ከኢትዮጵያ በሄዱ ዜጎች ላይ የሚደርሰው የሞትና እንግልት ኣደጋ ተነግሮ የሚያልቅ ኣይደለም። ይህ ሁሉ ሲሆን ታዲያ የወያኔ መንግስት ከነዚያ የባእድ መንግስታት ጋር ተባብሮ ስደተኞቹን ማስገደል፣ ማሳሰርና ወደ ሃገር ቤት መልሶ ማሰቃየት ካልሆነ በስተቀር ዜጎቼ ብሎ ደርሶላቸው ኣያውቅም።
በጥቅሉ ሲታይ በባእድ ኣገራት ውስጥ በኦሮሞና ሌሎችም ብሄር ተወላጅ ስራ ፈላጊ ስደተኞች ላይ እየደረሰ ላለው ሰቆቃ ዋነኛ ተጠያቂው ባእዳኑ መንግስታት ሳይሆኑ ራሱ የወያኔ መንግስት ነው። በበርካታ ምክንያቶች ተጠያቂ ይሆናል። በመጀመሪያ ደረጃ ስደተኞቹን ገፍቶ ከሃገር እንዲወጡ በማድረጉ ይጠየቃል። በሁለተኛ ደረጃ ስደተኞቹ በደረሱባቸው ኣገራት ሰብኣዊ መብታቸው ተከብሮ እንዲሰሩ በኤምባሲዎቹ ኣማካኝነት ክትትል ባለማድረጉ ተጠያቂ ይሆናል። ሶስተኛ ደግሞ ስደተኞቹ በሚኖሩባቸው ኣገራት ሰብኣዊ መብቶቻቸውን ሲገፈፉ ፈጥኖ ደርሶላቸው ተገቢውን እርምጃ ኣለመውሰዱ ተጠያቂ ያደርገዋል።
ከሁሉም በላይ ግን ስራ ፈላጊዎቹ ዜጎች በገዛ ኣገራቸው ላይ ሰርተው ራሳቸውን እንዲችሉ በማበረታታት ምትክ ተስፋ ቆርጠው ስደትን እንዲመርጡ መገፋፋቱ ትልቅ መንግስታዊ ጉድለት ነው። ዜጎቹ ኣገራቸውን ለቀው ኣንዳይሄዱ ለማድረግ ከፖለቲካ ተጽእኖ ነጻ የሆነ የስራ እድል ማመቻቸት መንግስታዊ ሃላፊነቱ ነበረ። ሁሉም ዜጎች በሚኖሩባቸው ክልሎች ከማናቸውም የፖለቲካ ኣመለካከቶች ነጻ የሆነ ሰርቶ የመሻሻል እድል ማግኘት መብታቸው ነበር። ወያኔ ያንን የዜግነት መብታቸውን ቀማ። ለምሳሌ የኦሮሞ ተወላጆች በክልላቸው ኦሮምያ ውስጥ ባለው የተፈጥሮ ሃብት ተጠቅመው ሰርተው መሻሻል ይችሉ ነበር። በእርሻ፣ በከብት ርቢ፣ በንግድ እንዲሁም በሲቪል ኣገልግሎቶች መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ መዋቅሮች ውስጥ ያላንዳች የፖለቲካ ተጽእኖ ተሰማርተው ራሳቸውንም ሆነ ኣገራቸውን መጥቀም ይችሉ ነበር። የወያኔ መንግስት ግን እነዚህን መሰል የስራ እድሎች ነጥቆኣቸው ለስደት ህይወት ዳረጋቸው። በስመ እንቬስተርነት የራሱን ካድሬዎችና ሰላዮች መልምሎ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ኣሸክሞ ክልሎች ላይ በማሰማራት የስራ እድሉን ነጠቃቸው።
የዚህ ችግር መንስኤ ራሱ የወያኔ መንግስት ኣድሎኣዊ ኣሰራር እስከሆነ ድረስ የችግሩ መፍትሄም በራስ ኣገር ላይ ሰርቶ የመኖርን መብት የቀማውን ስርኣት ታግሎ የራስን መብት ማስከበር ብቻ ነው። የነዚህ ስራ ፈላጊ ስደተኞች ችግር ላይ ላዩን ሲታይ የኢኮኖሚ ችግር ይምሰል እንጂ መሰረቱ ግን ኣገር ቤት ላይ የሚደርሰው የፖለቲካ ጫና መሆኑ ታውቆ የፖለቲካ መፍትሄ ሊያገኝ ይገባል። ጎሮቤት ኣገራትና መካከለኛው ምስራቅ ውስጥ ስራ ፍለጋ ሲንከራተቱ የተገደሉ፣ የተደበደቡ፣ ለኣካል ጉድለት የተዳረጉ፣ የታሰሩና በሃይል ተይዘው ወደ ኣገራቸው የተመለሱ የኦሮሞና ሌሎች ብሄሮች ተወላጅ የሆኑ ዜጎች በሙሉ ራሳቸውን መጠየቅ ያለባቸው ጥያቄም ይሄው ነው። ኦሮምያ ላይ ሌላው ሰርቶ በኣጭር ጊዜ ውስጥ ሚሊዮነር ሆነ ሲባል እኔ ለምን ኣገሬ ላይ ሰርቼ ማደግ ተሳነኝ? ለምን ለስደት ህይወት ተጋልጬ በባእድ ኣገር ላይ ተዋረኩ? የሚሉትን ጥያቄዎች ራሳቸውን ጠይቀው ምላሹንም ማግኘት ይገባቸዋል።
No comments:
Post a Comment