Sunday, December 8, 2013

የደህንነት አባሉ ተጨማሪ 11 ክሶች ቀረበባቸው!



<<>>>በርካታ ድርጅቶች በሽብር ላይ የሚያተኩር መጽሐፋቸውን በተጽዕኖ እንዲገዟቸው አድርገዋል
>>>>>ከቤተሰቦቻቸው ጋር በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብና ሃብት አፍርተዋል
>>>>>ሁለተኛ ተከሣሽ ደግሞ በመከላከያ ውስጥ ተቀጥሮ ሲሠራ ደሞዙ 523 ብር ሆኖ ሳለ፣ በ3 የንግድ ባንክ ቅርንጫፎች ከ150 ሺ እስከ 2 ሚሊዮን ብር ሲያንቀሳቀስ እንደነበር ተመልክቷል

ከቤተሰቦቻቸው ጋር በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብና ሃብት አፍርተዋል የቀድሞው የደህንነት አባልና የትግራይ ልማት ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ወልደስላሴ ወልደሚካኤል፤ ከቤተሰባቸው ጋር በመሆን ፈጽመውታል በተባለው የሙስና ወንጀል ተጨማሪ 11 ክስ ቀረበባቸው፡፡ ግለሰቡ ከእነ አቶ መላኩ ፈንታ ጋርም በሌላ መዝገብ መከሰሳቸው ይታወሣል፡፡ አቶ ወልደስላሴ፤ አሁን ለተጨማሪ ክስ የዳረጋቸውን ወንጀል ፈፀሙ የተባለው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት መ/ቤት ሠራተኛ በነበሩበት ጊዜ ሲሆን ከፊሉን ከወንድማቸው አቶ ዘርአይ ወ/ሚካኤል፣ ከእህታቸው ወ/ሮ ትርሃስ ወ/ሚካኤል እንዲሁም ከቅርብ ጓደኛቸው አቶ ዳሪ ከበደ ጋር በመመሳጠር፣ ከፊሉን ለብቻው እንደፈፀሙ ተገልጿል፡፡ ከትናንት በስቲያ ክሣቸው በንባብ የተሰማው አቶ ወልደስላሴ፤ በ1ኛነት የቀረበባቸው ክስ፤ የደህንነት መስሪያ ቤት ባልደረባ መሆናቸውን መከታ በማድረግ፣ በ2002 ዓ.ም “Terrorism in Ethiopia and the Horn of Africa” የተሰኘ መጽሐፋቸውን፣

ከመንግስት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ በየነ ገ/ስላሴ ጋር ያላቸውን መልካም ግንኙነት በመጠቀምና ግለሰቡን በማታለል፣ ኤጀንሲው በሚያስተዳድራቸው ብርሃንና ሠላም ማተሚያ ድርጅት፣ ቦሌ ማተሚያ ድርጅት እና አርቲስቲክ ማተሚያ ድርጅት ስፖንሰር አድራጊነት፣ 3ሺህ መጽሐፍት በ124,000 ብር እንዲታተሙ አስደርገው በመሸጥ ገንዘቡን ለግል ጥቅማቸው አውለዋል ይላል፡፡ በዚያው ክስ ላይ በ2ኛነት የቀረበው ክስ ደግሞ፤ ግለሰቡ በዚያው አመት ይህንኑ መጽሐፍ 10ሺህ ኮፒ ለማሳተም በሚል የመጽሐፉ ይዘት ከቴሌኮሙኒኬሽን ጋር ባልተገናኘበት እና የማስተዋወቅ ስራም ባልተሠራበት ሁኔታ የደህንነት አባልነታቸውን መከታ በማድረግ ከወቅቱ የቴሌኮምኒኬሽን ሃላፊ አቶ አማረ አምሣሉ ከ385ሺ ብር በላይ መቀበላቸውን ይጠቁማል፡፡

በዚሁ ክስ ላይ በ3ኛ እና በ4ኛነት በቀረቡት ክሶች፤ ግለሰቡ በኢትዮጵያ አትክልትና ፍራፍሬ ገበያ አክሲዮን ማህበር እንዲሁም በሙገር ሲሚንቶ ኢንተርፕራይዝ የነበራቸውን የቦርድ አባልነት እንዲሁም የደህንነት ሠራተኛነታቸውን መከታ በማድረግ፣ የአክሲዮን ማህበራቱ 310 መጽሐፍትን በ62ሺ ብር እንዲገዙ ካስደረጉ በኋላ፤ ገንዘቡንም መጽሐፍቱንም ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸው ተጠቅሷል፡፡ በመዝገቡ በ2ኛነት የቀረበውም ክስ ደግሞ ግለሰቡ የደህንነት ሠራተኛ መሆናቸው የፈጠረላቸውን ተሠሚነት እንደመልካም አጋጣሚ በመውሰድ፣ ወደ 26 የሚሆኑ ኩባንያዎችና ባለሀብቶች የተለያየ ብዛት ያላቸውን መጽሐፍት እንዲገዙ ካስደረጉ በኋላ፣ መጽሐፍቶቹን ሳያስረክቡ ለግል ጥቅማቸው አውለዋል ይላል፡፡ ከእነዚህ መካከል የአልሣም ኃላ.የተ.የግ ማህበር ባለቤት አቶ ሣቢር አረጋው፤ ያለፍላጐታቸው በሌላ መዝገብ ክስ በቀረበባቸው በአቶ ገብረዋህድ ወ/ጊዮርጊስ እና በባለሀብቱ በአቶ ነጋ ገ/እግዚአብሔር በኩል 500 መጽሐፍትን በመቶ ሺህ ብር እንዲገዙ ካስደረጉ በኋላ መጽሐፍቱን ለግላቸው አስቀርተው መጠቀማቸው፣ ጌታስ ትሬዲንግ 1500 መጽሐፍትን፣ ነፃ ፒኤልሲ 700፣ ካንትሪ ትሬዲንግ 300፣ ሐበሻ ካፒታል ሠርቪስ 50፣ አኪር ኮንስትራክሽን 100 መጽሐፍትን እንዲሁም በርካታ ድርጅቶችና ግለሰቦች የተለያየ ብዛት ያላቸውን መጽሐፍት እንዲገዙ ካደረጉ በኋላ፣ መጽሐፍቶቹን ሳያስረክቡ ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸው ተመልክቷል፡፡

በግለሰቡ ላይ በ3ኛነት በቀረበው ክስ፣ የተሰጣቸውን ሃላፊነት ያለአግባብ በመጠቀም በመዝገቡ ስሟ የተጠቀሰን ግለሰብ በመንግስት መኪና ቁልቢ ድረስ እንድትሄድና በተለያየ ጊዜ እንድትዝናና አስደርገዋል እንዲሁም ግለሰቧ ለነበረባት የፍትሃብሔር ክርክር የመ/ቤቱን ሠራተኛ መድበው፣ መደበኛ ስራውን ትቶ እንዲከታተል አስደርገዋል ይላል፡፡ በ4ኛ እና በ5ኛነት የቀረቡባቸው ክሶችም፤ ስልጣናቸውን መከታ በማድረግ፣ አቶ ሣቢር አርጋው የተባሉት ባለሃብት ጋ በመደወል፣ ለሚሠሩት ቤት ሴራሚክ እንደጐደላቸው በመንገር፣ ግለሰቡ በ65ሺህ ብር እንዲገዙላቸው ማስደረጋቸው እንዲሁም ከመጽሐፍቶቹ ሽያጭ መንግስት ይፈልገው የነበረውን ከ496ሺህ ብር በላይ ግብር አሳውቀው አለመክፈላቸው በአቃቤ ህግ የክስ ዝርዝር ላይ ቀርቧል፡፡ ቀሪዎቹ ክሶች ከቤተሰብ አባላቱ ጋር ተጣምረው የቀረቡ ሲሆን በመዝገቡ ከ6ኛ እስከ 9ኛ ክስ ሆኖ የቀረበው፣ አቶ ወልደስላሴ፤ 2ኛ ተከሣሽ የሆኑትን ወንድማቸው አቶ ዘርአይን የመኖሪያ ቤታቸው ወኪል በማድረግ፣ ቤቱ ከመኖሪያ ቤት ውጪ ለሆነ አገልግሎት እንዲውል ካደረጉ በኋላ፣ መንግስት ይፈልገው የነበረውን ከ126ሺ ብር በላይ ግብር በተገቢው መንገድ አሳውቀው አልከፈሉም፤ በዚህም የሃሰት ወይም አሳሳች መረጃ በማቅረብ ወንጀል ተከሰዋል ይላል፡፡ በተጨማሪም ከ119ሺ ብር በላይ የተርን ኦቨር ታክስ ግብርም አልከፈሉም ተብሏል፡፡

በሁሉም ላይ የቀረቡት ቀሪዎቹ ክሶች ምንጩ ያልታወቀ ሃብት ይዞ መገኘት የሚሉ ናቸው፡፡ 1ኛ ተከሣሽ ለወንድም እና እህቶቹ እንዲሁም ለቅርብ ጓደኛው ውክልና እየሰጡና ንብረትን በማስተላለፍ ዘዴ እየተጠቀሙ ሃብት አፍርተዋል ይላል፡፡ ምንጩ ያልታወቀ ሃብት ተብለው ከተጠቀሱት መካከልም በአቶ ወልደስላሴ እና በባለቤታቸው ስም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አምስት የተለያዩ ቅርንጫፎች ከ9ሺ እስከ 1 ሚሊዮን 5 መቶ ሺ ብር በማስቀመጥና በማንቀሳቀስ ሲጠቀሙ እንደነበር ተመልክቷል፡፡ ይህ ሲሆን የግለሰቡ ደሞዝ ከ1600 እስከ 6ሺህ ብር ነበር ብሏል አቃቤ ህግ፤ ሁለተኛ ተከሣሽ ደግሞ በመከላከያ ውስጥ ተቀጥሮ ሲሠራ ደሞዙ 523 ብር ሆኖ ሳለ፣ በ3 የንግድ ባንክ ቅርንጫፎች ከ150 ሺ እስከ 2 ሚሊዮን ብር ሲያንቀሳቀስ እንደነበር ተመልክቷል፡፡ ምንም የገቢ ምንጭ እንደሌላት የተገለፀው እህቱ እና ጓደኛውም በውክልና እና በማስተላለፍ ሂደቶች የእርሻ ልማት ኢንቨስትመንት እና በአዲስ አበባ፣ በመቀሌ እና በአክሱም ቦታ እና ቤት፣ እንዲሁም በባንክ የተለያየ መጠን ያለው ገንዘብ አስቀምጠው መገኘታቸው በአቃቤ ህግ የክስ ዝርዝር ተቀምጧል፡፡ በእለቱ ክሣቸውን ፍ/ቤቱ በንባብ ካሠማ በኋላ፣ 3ኛ እና 4ኛ ተከሣሽ ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ የአቃቤ ህግን መልስ መነሻ በማድረግ ውድቅ ካደረገ በኋላ፣ ተከሣሾች የሚያቀርቡትን መቃወሚያ ወይም መከራከሪያ ለመጠባበቅ መዝገቡን ለታህሣስ 7 ቀን 2006 ዓ.ም ቀጥሯል፡፡

No comments:

Post a Comment