Sunday, June 9, 2013

የለገደንቢ ወርቅ ሽያጭ ድራማ!!

የለገደንቢ ወርቅ ሽያጭ ድራማ!!


እ.አ.አ በ1997 በጨረታ ወደ ግል ንብረትነት ተዛወረ የተባለው የኦሮሞ ሀብት የተሸጠው 172 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ሽያጩ ተግባራዊ ከሆነ በኋላ ሽያጩን ተከትሎ በርካቶች አርረዋል፤ ተቃጥለዋል። “ዋይ ዋይ ወርቃችን” ብለው አንብተዋል። ህዝብ የፈለገውን ቢል ደንታ የሚሰጠው አካል ስለሌለ የለገደንቢ ወርቅ ማዕድን ከኦሮሞ ህዝብ እጅ በአዋጅ ተነጠቀ።
ሽያጩን እውን ያደረገው የኢትዮጵያ የፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ቦርድ ሰብሳቢ የነበሩት የወቅቱ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሀሰን አሊ ሲሆኑ፣ የአቶ ስዬ አብርሃ ወንድም አቶ አሰፋ አብርሃ የኤጀንሲው ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ነበሩ። ሁለቱም ባለስልጣናት ዛሬ ሃላፊነት ላይ የሉም። ስለ እውነትና ስለአገር ሲሉ የሚያውቁትን ለመተንፈስ እስከዛሬ ቢጠበቁም ያሉት ነገር የለም። ሃሰን አሊ ሲኮበልሉ፣ አቶ አሰፋ አብርሃ ከወንድማቸው ጋር በሙስና ተወንጅለው የወህኒ ቤት ጊዜያቸውን አጠናቀው እየኖሩ ነው።
ምዕራብ ሃረርጌ አሰበ ተፈሪ መምህር የነበሩትና ኢህአዴግን መንገድ ላይ የተቀላቀሉት ሀሰን አሊ ካገር መኮብለላቸውን ተከትሎ የተለያዩ መረጃዎች ይወጡ ነበር፡፡ በርካቶች ጉዳዩን ከኦነግ ጋር ቢያያይዙትም “ካገር ውጡ ተብለው፣ ሀብትና ንብረት ተዘጋጅቶላቸው ኮብልለዋል” የሚል መረጃ ለባለስልጣናትና ለባለሃብቱ ቅርብ ነን ከሚሉ ወገኖች እንሰማ ነበር። በወቅቱ ኦሮሚያ ክልል አስተዳደር ውስጥ በነበረኝ ሃላፊነት ሳቢያ ከሰማኋቸው መረጃዎች ውስጥ ሃሰን አሊ “ውጡ” ተብለው እንደ ኮበለሉ የሰማሁት መረጃ ካለኝ ሃላፊነት ጋር ተዳምሮ እንዳጣራው ወሰንኩና ጊዜ ሰጥቼ አነፈንፍ ገባሁ።
የሌሎችን ባላውቅም እንደ ኦሮሞነቴ የለገደንቢ ወርቅ ማዕድን ውድ ንብረት ለሼኽ መሃመድ ሁሴን አላሙዲ መሸጡ ሁሌም ያንገበግበኛል። ሽያጩን አስመልክቶ የተለያዩ ጽሁፎች ቢወጡም እኔ ካሰባሰብኩት መረጃና እውነት ጋር የሚመጣጠን መስሎ ስላልታየኝ የድረገጽ ጋዜጣ ለመተንፈስ ወሰንኩ።
ሼኽ መሐመድ አላሙዲና ሃሰን አሊ እንዴት ተዋወቁ?
ሼኽ መሀመድ አላሙዲና ሀሰን አሊን እንዳስተዋወቃቸው የነገረኝን ሰው ባንድ አጋጣሚ የማወቅ እድል አጋጥሞኝ ነበር። ተግባሩ ብዙም ደስ ስለማያሰኝ ፊት እነሳው ነበር፡፡ ባለስልጣናትን በገንዘብ እየደለለ ሲሰርቅ ብዙ ጊዜ ስለማውቅ አልወደውም ነበር። የራሱን ትልቅነት ለመግለጽ ድንገት ቢሮዬ በመጣበት ወቅት የነገረኝ ፍንጭ ትዝ ሲለኝ ላገኘው ወሰንኩ። ይህ ሰው ባለኝ ሃላፊነት እንደፈለገኝ ላገኘው ስለምችል፣ እሱም ለሚሰራው ድለላና አየር ባየር ንግድ እኔ ከፈለኩት ቅር ስለማይለው ፊት ነስቼው ያቋረጥኩትን ግንኙነት እንደገና መቀጠል ብቸኛ አማራጬ ሆነ፡፡ይህን ሰው ከተጠቀሙበት በኋላ ወርውረውት በነበረበት ወቅት ላይ ስላገኘሁት የፈለኩትን ለማግኘት አጋጣሚው ተመቻቸልኝ፡፡
ቀደም ሲል ሃሰን አሊን ያውቃቸው እንደ ነበር፣ አብረው ሃድራ እንደሚያሞቁ፣ የፈለገውን ነገር ማድረግ ከፈለገ ሃድራው በሚሞቅበት ወቅት እዛው በሙቀት እንደሚያከናውኑ አውግቶኛል። ለዚህ ጽሁፍ ስለማይጠቅም እንጂ በርካታ ታላላቅ ጉዳዮች ቢሮ ውስጥ ሳይሆን በተፈረሸ መደብ ላይ እንደሚከናወን በስፋት ስም እየጠቀሰ ነግሮኛል። እንግዲህ ይህ ሰው የ“ባለሃብቱ” ወዳጅ ነበር። ለዚያውም የመጀመሪያ!
በዚሁ ሽርክናቸው ሰውየው ሃሰን አሊን መተዋወቅ እንደሚፈልጉ ባሳወቁት መሰረት ሃሰን አሊን በመያዝ ሳር ቤት አካባቢ አገናኛቸው። ባለሃብቱ በወቅቱ ብዙም የሚያውቃቸው ባልነበረበት ወቅት ሃሰን አሊን አስቀድመው ተወዳጁ። በመኖሪያቤት ሃድራ ላይ የተመሰረተው ወዳጅነት ጠበቀ። በኦሮሚያ በኩል አድርገው ዋናውን ሳሎን ወረሱ።
ሀሰን አሊ ከኦሮሚያ ፕሬዚዳንትነታቸው ለቀው ስደትን ለምን መረጡ?
አሰበ ተፈሪ የሁለተኛ ደረጃ መምህር እያሉ ወያኔ ወደ ምስራቅ ኢትዮጵያ በረዣዥም በአለም የምግብ ድርጅት ሽንጣም የጭነት ተሽከርካሪዎች በሸራ ተሸፍነው ቀለሃ ሳያባክኑ ወደ ሃረርና ድሬዳዋ ሲተሙ ቆቦ የምትባል የመስመር ከተማ ላይ ሆኜ የመከታተሉ እድል ነበረኝ፡፡ ወያኔ የሀረርንና የድሬዳዋን ከተማ ለመያዝ ስትሮጥ አሰበ ተፈሪ ከተማ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃትምህርት ቤት ከአቶ ሀሰን አሊ ጋር ተገናኙ፡፡ ብዙም ሳይቆይ ሀሰን አሊ የክልሉ ፕሬዚዳንት ሆኑ፡፡ አስተማሪው ፕሬዚዳንት በስልጣን በቆዩባቸው ጊዜያት ከሚታሙባቸው ከፍተኛ ሙስናዎች መካከል፣ ባሌ ውስጥ ተከስቶ በነበረው የዋና ከተማነት ጥያቄ ተከትሎ የተቀበሉት ብር ነው። የባሌ ሮቤ ነጋዴዎች ሮቤ በዋና ከተማነት እንድትቀጥል ያሰባሰቡትን አንድ ሻንጣ ብር በስጦታ አቅርበውላቸው ነበር። ያረፉበት ቤት ድረስ የቀረበላቸው ስጦታሮቤን በዋና ከተማነት ጸንታ እንድትቆይ ወሰነ። ገንዘብ ተናገረ። ከአገር የመኮብለላቸው ጉዳይ ከዚሁ ጋር ተያያዥ ነው ቢባልም በፖለቲካው መስመር ደግሞ ኦነግ ናቸው የሚል ሰፊ ሃሜትነበረባቸው። እኔ ባካሄድኩት ማጣራትና በሰበሰብኩት መረጃ መሰረት ቀደም ሲል የጠቀስኩዋቸው ጉዳዮች እንዳሉ ሆነው፣ አቶ ሀሰን አሊ በለገደንቢ ወርቅ ሽያጭ በሙስና መጨመላለቃቸው ለመኮብለላቸው ዋናው ምክንያት ስለመሆኑ ሚዛን የደፋ ምርመራ አካሂጃለሁ፡፡
የለገደንቢን ወርቅ ማዕድን ለመሸጥ ወጥቶ በነበረው ጨረታ የተለያዩ ኩባንያዎች ቢሳተፉም ሼክ መሀመድ አላሙዲ ያሸነፉበትድራማና የሀሰን አሊ ወደ አሜሪካ መኮብለል በተመለከተ ያሰባሰብኩትን መረጃ ከዚህ እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡ ለራሴና ለወዳጆቼ ደህንነት ስል ስም ከመጥቀስ ግን እቆጠባለሁ፡፡
ሃሰን አሊ የቦርድ ሰብሳቢ ሆነው የሚመሩት የፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ የለገደንቢን ወርቅ ሽያጭ ጨረታ ከማስፈጸሙ በፊት ለገደንቢን አስመልክቶከፍተኛ የማባበል ስራ ተሰርቷል። በየጊዜው ሲደረጉ የነበሩ ማባበሎችን ይከታተል የነበረው የመረጃ መነሻ እንዳስረዳኝ ለገደንቢ እንደ መስቀል ሰንጋ ጠልፎ የተበለተው አስቀድሞ ነው። ኢህአዴግ በተለይም ህወሃቶችከኢትዮጵያ ኪስ የሚወስዱትን ንብረት ህጋዊ ለማስመሰል ያቋቋሙት ይህ ኤጀንሲ በቁንጮ አመራሩ መመሪያ ሰጪነት ባካሄደው ጨረታ የደቡብ አፍሪካ ኩባንያዎችም ተሳትፈው ነበር።
አንድ ቀን እዛው ቤት ውስጥ እንደተለመደው ሃድራው እየሞቀ በጨረታው የተሳተፈ የደቡብ አፍሪካ ኩባንያ የተሻለ ገንዘብ ማስገባቱ ባለሃብቱ ጆሮ ይደርሳል፡፡ ኩባንያው ያስገባው ገንዘብ መጠን ይገለጽላቸዋል፡፡ መጀመሪያ ያስገቡት ሰነድ ተቀይሮ ሌላ ሰነድ እንዲያስገቡ በተነገራቸው መሰረት አዲስ ሰነድ እንዲዘጋጅ ያደርጋሉ፡፡ በዚህ ድራማ ለገደንቢ ወርቅ ማዕድን ከኢትዮጵያ ህዝብ ሀብትነት ወደ ሼክ መሀመድ አላሙዲ ንብረትነት በ1997 ለስምንት ዓመት ተዛወረ፡፡
በጉጂ ዞን ሻኪሶ ወረዳ ሳካሮ በተባለው ቦታ የተሰራው ይህ አዲስ 4ኪሜ የዋሻ መንገድ ቀጭን ረጅም ጥቅልል ብረት ከምድር በታች እስከ 70ሜትር ይዘልቃል፡፡
በዓመት 3.5 ቶን ወርቅ በአማካይ ሲያመርት ቆይቶ ምርቱን በማሳደግ በአሁኑ ሰዓት ከ4.0 ቶን በላይ ማሳደጉን ይፋ ያደረገው ሚድሮክ ጎልድ በዚህ ዓይነት አሳፋሪ ድራማ ወደ ግል ይዞታነት ከተዛወረ በኋላ ሀሰን አሊ አገር ጥለው እንዲወጡ ተወሰነባቸው፡፡ የሽያጩ ድራማ ደብዛ መጥፋት ስላለበት ሀሰን አሊ በኦነግ ስም ካገር እንዲኮበልሉ ሁሉም ነገር ተዘጋጅቶ ከተጠናቀቀ በኋላ አሜሪካ ለስራ በሚል ሰበብ እንዲሄዱ ተደርጎ በዛው ቀሩ፡፡ አሜሪካን አገር ሱፐር ማርኬትና ነዳጅ ማደያ ተገዝቶላቸው ስለነበር ከነቤተሰቦቻቸው ወደ ንግድ ዓለም መግባታቸው ተሰማ። አሜሪካ ተገኝቼ ማጣራት ባልችልም አደራውንእዚያው ለምትኖሩ ታጣሩትና ትጎለጉሉት ዘንድ አሳስባለሁ። ምንም በሉ ምን የኢትዮጵያው “ለገደንቢ” የግለሰብ “ሚድሮክ” የሆነው በተፈረሸ ፍራሽ ላይ ነው – በምርቃና!!
ከ2005 በኋላ ለገደንቢ ወርቅ የማን ይሆናል?
ሚድሮክ ጎልድ ይፋ እንዳደረገው ሃያ ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ዘመናዊ መሳሪያ ተገዝቶ ወርቅ የማምረቱ ስራ እየተከናወነ ነው፡፡ በማስፋፊያ በተከለሉ ቦታዎች ላይ ከ4.7 እስከ 6.52ቶን የሚደርስ ወርቅ በዓመት ለማምረት የተጀመረው ስራ ውጤት ማሳየት ጀምሯል፡፡ ስለማስፋፊያ ስራው አዲስ ስምምነት መንግስትም ሆነ ማዕድን ሚኒስቴር ያሉት ነገር የለም፡፡ ሚድሮክ ከኮንትራት ዘመኑ (2005) በማለፍ እስከ 2020 በያዘው ዕቅድ ከ70 ቶን በላይ ወርቅ ለገበያ በማቅረብ ለመሸጥማቀዱን በመንግስት ሚዲያ ይፋ አድርጓል፡፡ 1.6 ቢሊዮን ዶላርየተጣራ ትርፍ እንደሚያገኝም አፉን ሞልቶ ተናግሯል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን አገርምን ታገኛለች በሚለው ጉዳይ ላይ ጥያቄ ማንሳትሃጢያት ነው፡፡ያስገድላል፣ ያሳስራል፣ ያስደበድባል …
ለመሆኑ ከ1997 ለስምንት ዓመት ኮንትራት የተሰጠው ለገደንቢ ወርቅ እስካሁን በአላሙዲ እጅ እንዲቆይ የተደረገበትውልና የውሉ ዝርዝር ለምን ምስጢር ሆነ? በምን ዓይነት አዲስ ውልና ክፍያ ተጨማሪ ቦታ ተከለለ? በምን ያህል ዶላር የሽያጭ ውልና መግባቢያ ባለሃብቱ ወርቁን እንዲዝቁ ተወሰነ? ማዕድን ሚኒስቴር አለሁ ቢል ወይም ራሱ ሚድሮክ በግልጽ በድረ ገጹ ቢያሰፍረው ቢያንስ ቂማችን ይቀንስ ነበር።
ለወትሮውም በብድር እንደተሸጠ የሚነገርለት ለገደንቢ ወርቅ ማምረቻ ብድሩ ሙሉ በሙሉ መከፈሉ በ
ይፋ ባይገለጽም ሀብቷን በድራማ ጨረታ በብድር የሸጠችው ኦሮሚያ ህዝቧ ከሃብታቸው ድርሻቸው 2% ብቻ ነው፡፡ከሮያሊቲክፍያ ማግኘት የሚገባትን ሚጢጢ ገንዘብ እንኳን ባግባቡና በወቅቱ አታገኝም፡፡ የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስትር አቶ ሱፍያንየመንግስት የልማት ድርጅቶች ሃላፊዎችን ሰብስበው ሲያነጋግሩ ‘’ለመሆኑ ሚድሮክ ጎልድ ላይ ያለን ድርሻ ስንት ነው? ማስገባት ያለባቸውን ገንዘብስ ይከፍላሉ?” በማለት መጠየቃቸው በወርቅ ማዕድኑ ዙሪያ ያለውን እንቆቅልሽ ወለል አድርጎ እንደሚያሳይ ስብሰባው ላይ የተሳተፉ በወቅቱ የተናገሩት ነው።
በቀኝ በኩል የሚታየው አርቲፊሻልና በኬሚካል የተፈጠረ ሐይቅ ሲሆን በግራ ደግሞ ያለው የተፈጥሮ ሐይቅ ነው፡፡ አርቴፊሻሉ ሐይቅ ቀለም የተከሰተው በቁፋሮ የሚወጣውን ወርቅ ለማጣራት ጥቅም ላይ በሚውለው ኬሚካል አማካኝነት ነው፡፡
ይህ ብቻ አይደለም ከለገደንቢ ከርስ የሚጣራው የኦሮሚያ ደም /ወርቅ/ ወደ ገበያ ሲሄድ ቁጥጥር አለመደረጉ ሌላው አስገራሚ ድራማ ነው፡፡ አገርና ህዝብ እመራለሁ የሚለው ኢህአዴግ ሚድሮክ በቀጠራቸው ባንዳዎች አማካይነት ወርቁን በሉፍትሐንሳ አውሮፕላን ብቻ የሚያመላልሱት ለምንድ ነው? ለሚለው ጥያቄ መልስ የለውም፡፡ በሌላ አነጋገር አገር የሚገባትን የሽያጥ ታክስም ወደ ውጪ በሚላከው መጠን መሰረት እየተሰላ አይከፈልም። በእንዲህ ዓይነት መልኩ በአገራችን ኢኮኖሚና ህልውና ላይ ይጋለብበታል፡፡ ሚድሮክ ወርቅ አንዱ ማሳያ እንጂ ማጠቃለያ ግን አይደለም፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወርቁን ወደ ሚላክበት ስፍራ በማመላለስ የትራንስፖርት ንግድ ለመነገድ ጠይቆ “አይሆንም” ነው የተባለው ለምን? ኢህአዴግና ባለስልጣናቱ ለዚህም መልስ የላቸውም፡፡ አገር ወዳዶች ግን መልሱን ያውቁታል፡፡ ልባቸው እየደማ፣ ኅሊናቸው እየቆሰለ ፣ አገራቸው ስትታረድ የሚመለከቱወገኖች ለምንና? እንዴት? ብለው ሲጠይቁ አሁንም ይገደላሉ፣ይታሰራሉ፣ ይገረፋሉ፣ህዝብን በማነሳሳትና በሽብርተኛነት ወንጀል ይከሳሳሉ፡፡ እስከ ህልፈታቸው ወህኒ እንዲጣሉ የተሸጡ ወንድሞቻቸው ይፈርዱባቸዋል፡፡ በሃገረ ማሪያምና በቡሌ ሆራ ወረዳ የሆነው ይኸው ነው!
ሚድሮክ ወርቅ እያግበሰበሰ ያለው ሃብት ስለጣፈጠው በግልጽ ባልተቀመጠ ውል ግዛቱን እያስፋፋ የአካባቢውን አርሶ አደሮች ሲያፈናቅል የቡሌ ሆራና የሀገረ ማሪያም ነዋሪዎች ከልማቱ ተጠቃሚ አለመሆናቸውንና ባካባቢው ላይ እየደረሰያለው ብክለት ጉዳት እያደረሰባቸው መሆኑን ገልጸው በመቃወማቸው በሽብርተኛነት ወንጀል ተከሰዋል፡፡
ጥር 5 ቀን 2002 በሻሸመኔ ምድብ ችሎት በሽብርተኛነት ወንጀል ክስ የተመሰረተባቸው የአካባቢው ተወላጆች ላይ የደረሰውን መከራ የሰብአዊ መብት ጉባኤ 34ኛ መደበኛ ጉባኤ ህዳር 8 ቀን 2003 ዓም ስም በመዘርዘር ይፋ አድረጓል፡፡ ከሳምንት በላይ ትምህርት ተቋርጦ በርካታ ተማሪዎችና ነዋሪዎችም ታስረው እንደ ነበር የሚታወስ ነው፡፡
የፌዴራሉን እንተወውና ኦሮሚያና ሼኽ መሃመድ አላሙዲ በምን ምክንያት ተጣሉ? በወቅቱ የተቀሰቀሰው ተቃውሞና ኦህዴድ፣ወደፊት የባለሃብቱና የኦሮሚያ እጣ ፈንታ ምን ይመስላል? በሚሉት ርዕሶች ዙሪያ ተጨማሪ ዘገባ ይዤ እመለሳለሁ። በመግቢያዬ እንዳልኩት ዋይ ዋይ ወርቃችን!!


Juukii Bareentoo 

No comments:

Post a Comment