ከጥቂት ጊዜያት በፊት BecauseIamOromo በሚል ርእስ አለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተቋም አምነስቲ ኢንተርናሽናል በኦሮሞ ወጣቶች አራማጆች እና ፓለቲከኞች ላይ የሚደርሰውን ሰፊ የመብት ጥሰት በዝርዝር የሚያሳይ ሪፓርት ማውጣቱ ይታወሳል፡፡ ይህ ሪፓርት በተደጋጋሚ የምንሰማቸው የነበሩትን የኦሮሞ ወጣቶች ላይ የሚደርሱ የመብት ጥሰቶቸን በአስደንጋጭ ሁኔታ እና በሚገባ የዘገበ ነው፡፡ ይህ የመብት ጥሰት ዘገባ በተለያዩ አካላት ርእሰ ጉዳይ ተደርጎ ቢነሳም በቂ ውይይት ሊደረግበት ተጨማሪ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል በሚል እሳቤ ከህዳር 4 እስከ 6 ሶስት ቀናት የሚቆይ የበይነ መረብ ዘመቻ አዘጋጅተናል፡፡ ይህ ዘመቻ የሪፓርቱ ርእስ በሆነው ኦሮሞ በመሆኔ (#BecauseIamOromo) በሚል መሪ ቃል ይካሄዳል፡፡
የዚህ በይነ መረብ ዘመቻ ዋና አላማ በኦሮሞ ህዝብ ላይ በመንግስት በሰፊው ያለማቋረጥ እየተካሄደ ያለው የሰብአዊ መብት ረገጣ ለማውገዝ ፣ በመብት ረገጣው ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች አጋርነታችንን ለማሳየትና በጨቋኙ ስርአት በኦሮሞ ህዝብ ላይ እየደረሰ ላለው ቀጣይ የመብት ጥሰት ዝም መባል የማይገባው አገራዊ ጉዳይ አንደሆነ ለማሳየት ነው ፡፡ በዚህ ዘመቻ በዘጋቢ ሪፓርቱ ላይ በሰፊው የተጠቀሱ የኢህአዴግ መንግሰት የፈጸማቸውን የመብት ጥሰቶችንም ለማጋለጥ እና ለማሳወቅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብለን እናምናለን፡፡ በዚህ ዘመቻ ማስተላለፍ የምንፈልገው መልእክት ግልጽ ነው፡፡ የህዝቦች ወንድማማችነት በጨቋኝ ስርአት ውስጥ ጠንክሮ መታየት እንደገባው በአንድ ብሄር ላይ የተነጣጠረ የመብት ጥሰትም የሁሉም ኢትዮጲያውያን ጉዳይ መሆኑን! አንድ አካል ሲነካ መላ ሰውነትን እንደሚያመው ሁሉ ገዢዎቻችን ለይተው የሚያደርሱት ጭቆና የሁላችንም ህመምና ጉዳይ መሆኑን ለማሳየት በዚሀ ዘመቻ ላይ በንቃት እንድትሳተፉ በአክብሮት ተጋብዛችኋል፡፡
ፌስቡክና ትዊተር በዋናነት የዘመቻው ቦታዎች ሲሆኑ፣ የዘመቻው ተሳታፊዎች በሙሉ #BecauseIamOromo መሪ ቃልን አንዲጠቀሙ ከዘጋቢ ሪፓርቱ እና ከሪፓርቱም ውጪ የሚያቋቸውን ታሪኮች አጭር ጽሁፎች(ስታተሶች) እንዲሁም የተሰማቸውን ስሜት በመግለጽ ለዘመቻው የተዘጋጁ ፕሮፋይል ፎቶዎቸን እና የሽፋን ምስሎችን በመጠቀም በዘመቻው ንቁ ተሳታፊ አንዲሆኑ በአክብሮት አንጋብዛለን፡፡ በሶስቱ ቀን የዘመቻ ቆይታ ለዘመቻው ተብሎ የተከፈተው ኤቨንት ገጽ ላይም ሀሳቦችን በመለዋወጥ እና ስለዘመቻው ያላችሁን ሃሳብ አንድትገልጹ በአክብሮት ጥሪ እናስተላልፋለን፡፡
አንወያይ ሃሳብና ስሜታችንን እናካፍል ጉዳያችን መሆኑን አጋርነታችንን እናሳይ!
#ኦሮሞ_በመሆኔ #OromooTauukoof #BecauseIamOromo
No comments:
Post a Comment