Thursday, November 15, 2012

የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አዲስ አባላት

መቀመጫው ጄኔቫ ለሆነው ምክር ቤት  ከተመረጡት አሥራ ስምንት ሃገሮች ብቃት ያላቸውና መመዘኛውን የሚያሟሉት አንድ ሦስተኛ ብቻ መሆናቸውን የመብቶች ተሟጋቾቹ ገልፀዋል፡፡

ሂዩማን ራይትስ ዋች ከተመረጡት ሃገሮች መካከል ኢትዮጵያን አንስቶ በሰብዓዊ መብቶች ረገጣ ከሚታወቁ ሃገሮች አንዷ እንደሆነች አመልክቷል፡፡ 

አርባ ሰባት መቀመጫዎች ያሉት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አዘውትሮ የሚወቅሰው ለእሥራኤል ጉዳይ ልዩ ትኩረት ይሰጣል እየተባለ ነው፡፡ ከዚያ ጋር በሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ታሪካቸው ላይ እድፍ ብጤ አይጠፋቸውም የሚባሉ ሃገሮች አባላቱ የመሆናቸው ጉዳይም ሌላው ነቀፌታ የሚያደርስበት ነጥብ ነው፡፡ በምክር ቤቱ ውስጥ ያሉት መቀመጫዎች የሚደለደሉት በአካባቢያዊ የአመዳደብና የውክልና ሥርዓት ነው፡፡
በዘንድሮው የምክር ቤቱ አባላት አሰያየም ላይ እውነተኛ ፉክክር የተካሄደው ከአምስት መቀመጫዎቹ ሦስቱን እንዲሞላ በተጠየቀውን “የምዕራብና ሌሎች” በሚባለው ምድብ ውስጥ ነው፡፡
የሂዩማን ራይትስ ዋች የተባበሩት መንግሥታት ዳይሬክተር ፊሊፕ ቦሎፒዮን: የምክርቤቱ አባል ለመሆን ፉክክር ያለመኖሩና የሰብዓዊ መብቶች አያያዛቸው ጥያቄ ውስጥ የሆነ ሃገሮች አባል የመሆናቸው ጉዳይ ቅሬታን የሚያስነሣ መሆኑን በመጥቀስ ነቅፈዋል፡
ቦሎፒዮን የኢትዮጵያን የመብቶች አያያዝ ታሪክ አንስተውም ወቅሰዋል፡፡

“የኢትዮጵያ መንግሥት - አሉ ቦሎፒዮን - ይህንን አጋጣሚ ትርጉም ያላቸውን እርምጃዎች ለመውሰድ ሊጠቀምበት ይገባል፡፡ ለምሣሌ ሃሣብን በመግለፅና በመሰብሰብ ነፃነት፣ ወይም የፀጥታ ኃይሎቹን በተጠያቂነት በመያዝ፣ በተጨማሪም ምናልባትም አሁን እየተቀላቀለው ካለው የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ጋር በእውነተኝነት መተባበር መጀመር አለበት፡፡”







No comments:

Post a Comment